ኢሬቻ የሰላም፣ የእርቅ፣ የምሰጋና የአንድነት እና የህዝቡ ሀብት በመሆኑም ልንጠቀምበት ይገባል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ በዓል የሰላም፣ የእርቅ፣ የምስጋና የአንድነት እና የህዝቡ ሀብት፥ ትልቅ የቱሪዝም ምንጭ በመሆኑ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንደገለጹት፥ የኦሮሞ ህዝብ የዳበረ ባህል እና እሴት ያለው፣ የገዳ ሰርዓት አስተዳደርን የፈጠረ፥ የሚተዳደርበትና የሚያስተዳድርበት፣ ሁሉን አቀፍ ፍልስፍና፣ የፈጣሪን እና የተፈጥሮን ሚዛን በመጠበቅ የዕለት ተዕለት ኑሮውን የሚከውን ህዝብ ነው።
አቶ ሽመልስ እንዳሉት፥ ክረምቱ አልፎ ብራ ሲመጣ፣ በጋው ሄዶ በልግ ሲሆን የኦሮሞ ህዝብ የመጪው ዘመን ብሩህ ተስፋ የሆነውን ኢሬቻን ያከብራል፡፡
ኢሬቻ ከጨለማ ወደ ብርሃን መውጣትን እንደሚያሳይ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ብራ አዝርት አብቦ የሚያሸትበት ወቅት፣ ወንዝ የሚቀንስበት፣ተራርቀው የከረሙ ዘመድ- ወገኖች የሚገናኙበት በመሆኑ የሰው ልጆች ተስፋ መታደስ በብዛት የሚታይበት ነው ብለዋል፡፡
ለዚህ ነው ኦሮሞ እርጥብ የሰርዶ ሳር እና አበባ ይዞ በመልካ ኢሬፈና የሚከናወን፤ ሰርዶ ትልቅ ትርጉም ያለው፥ ከሳሮች ሁሉ ችግር የሚቋቋም የሚችል፤ ጠንካራና እንደ ህይወት ምልክት የሚታይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢሬቻ የምስጋና፣ የእርቅ፣ የፍቅር እና የአንድነት በዓል ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ያለምንም ልዩነት በጋራ በመሰባሰብ የሚከበር ነውም ብለዋል፡፡
መሬሆ! መሬሆ! በማለት የጋራ የምስጋና ድምጽ የሚያሰሙት አንድ ቃል መናገርን እንደሚያመለክትም አብራርተዋል አቶ ሽመልስ በመልዕክታቸው፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የሚሳተፉበት አቃፊና የኦሮሞን ሀዝብ ትልቅነት የሚያሳይ በዓል እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
ኢሬቻ የሰላም፣ የእርቅ፣ የምሰጋና የአንድነት እና የህዝቡ ሀብት እንዲሁም ትልቅ የቱሪዝም ምንጭ በመሆኑም፥ በአግባቡ ልንጠቀምበት፥ ክልሉን እና ሀገርን ልናስተዋውቅበት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!