Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ የተሰጣቸውን የውጭ አገር ዜጎች አስመልክቶ ፈጽመዋል ያለውን ህገ ወጥ ተግባራት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያየዩ የተመድ ድርጅቶች ተቀጠረውና የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት እንዲሰጡ በሚሰሩበት ወቅት ከሙያቸው ሥነ ምግባር ውጭ ተንቀሳቅሰዋል ያላቸውንና ሰባት ግለሰቦች የፈጸሟቸውን ሀገ ወጥ ተግባራት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል።
ሚኒስቴሩ ዛሬ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ መሰረት በተለያየዩ የተመድ ድርጅቶች ተቀጠረው በሚሰሩበት ወቅት ከሙያቸው ሥነ ምግባር ውጭ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉት ሰባት ግለሰቦች ከፈጸሟቸው ህገ ወጥና ኢ -ሥነ ምግባራዊ ተግባራት መካከል
1. ለተቸገረው ህዝብ ተብሎ የመጣን የሰብዓዊ ድጋፍና ዕርዳታ ለህወሃት አሳልፎ መስጠታቸው
2. ከመንግስት ጋር የተደረገን ስምምነት መጣሳቸው
3. የመገናኛ መሳሪዎችን ህወሃት እንዲጠቀምበት ማስተላለፋቸው
4. ሰብዓዊ ድጋፎችን ይዘው ወደ ትግራይ የገቡና ሳይመለሱ የቀሩ 400 ተሽከርካሪዎች በህወሃት ቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ለወታደራዊ ተግባር ተግባራትና ለታጣቂዎቻቸው ማመላለሻ መዋላቸውን እያወቁ እንዲመለሱላቸው ለመጠየቅ ተደጋጋሚ ቸልተኝነት ማሳየታቸው
5. ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨታቸውና ሰብዓዊ ድጋፍን ለፖለቲካ ዓላማ እንዲውል ማድረጋቸው የሚጠቀሱ ናቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራች አባል እንደመሆንዋ፥ ለድርጅቱ ቻርተር ያላትን ቁርጠኝነት ለዓመታት በተግባር ማሳየቷን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የተመድ ኤጀንሲዎች በተለይም በሰብዓዊ ድጋፍ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ለሚሊዮኖች የህይወት አድን አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር አስታውሷል።
ኢትዮጵያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እነዚህ የተመድ ድርጅቶች ላደረጉት ሰብዓዊ ድጋፍ ሁሉ ምስጋና እና አድናቆት የምትሰጥ አገር እንደሆነችም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስረድቷል::
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን ማጠናከርና ዕርዳታ ለሚያስፈልገው ህዝብ ህይወት አድን ድጋፍ ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከእነዚህ የተመድ ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መፈራረሙን የጠቀሰው ሚኒስቴሩ፥ ይህ ስምምነት በድርጅቶቹ አመራሮችና ሰራተኞች የተጣሰ መሆኑን አስረድቷል።
ከተመደቡበት ዓላማና ተግባር ውጭ በመንቀሳቀስ የሙያ ሥነ ምግባራቸውን መጣሳቸውንና ህገ ወጥ ተግባር መፈጸማቸውንም አብራርቷል።
በሰብዓዊ አገልግሎት ሥራ ላይ ተሰማርተው ሳለ፣ ከፍተኛ የሙያና የህግ ጥሰት በፈጸሙ በእነዚህ የውጭ አገር ዜጎች ላይ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተወሰደው ከሀገር የማስወጣት ዕርምጃ ህጋዊና ተገቢ መሆኑንም አስምሮበታል።
በሌላ በኩል ይህ ውሳኔ ያላስደሰታቸው የተወሰኑ አገራት፣ ጉዳዩን የጸጥታው ምክር ቤት በፍጥነት እንዲመለከተው ለማድረግ ባደረጉት ጥረት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቅሬታ እንደተሰማትም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
አክሎም የጽጥታው ምክር ቤት፥ ከጀርባው የፖለቲካ ፍላጎት ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ውድቅ እንደሚያደረገው ተሰፋ አለን ብሏል ።
በዚህ ውሳኔ ቀደም ብሎ ሲደረግ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ ችግር እንደማይገጥመውም እርግጥኞች ነን ሲል ጠቁሟል፡፡
በርግጥ ህወሓት ንዑሃንን ማጥቃጥ፣ከቀዬያቸው ማፈናቀል፣እንስሳትን መግደል፣ የኢኮኖሚ አውታሮችን ማውደም፣ከ400 በላይ የእርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት በማዋል የድጋፍ ሂደቱን አስቸጋሪ ማድረጉን ቀጥሎበታል ብሏል መግለጫው፡፡
አንዳንድ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካለት እንዲህ ዓይነቱን ተግባር በአሸባሪው ህወሃት በኩል ለማስፈጸም እና በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሉዓላዊ መብቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ችግር ላይ ለመጣል መሞከራቸው እንደማይሳካ ጠቁሟል።
በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የሕዝባችንን ስቃይ የማቃለል ተግባር አላማቸው ከሆኑት ከተባበሩት መንግስታት እና ከኤጀንሲዎቹ ጋር ተባብረን መስራታችንን እንቀጥላለን ሲልም አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ከሌሎች ተቋማት ጋር የሚደረገው ትብብር ቀጣይነት እንደሚኖረው የኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ ማድረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቆ፥ ይህ የሚሆነው ግን እንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማይዳፈሩ፣ ለብሔራዊ ደህንነታችንና ጥቅሞቻችን ስጋት ካልሆኑ ብቻ ነው ብሏል።
በተለያየዩ የተመድ የሰብዓዊ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጠረውና በሃላፊነት ተመድበው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሰሩበት ወቅት ከሙያቸው ሥነ ምግባር ውጭ ተንቀሳቅሰዋል፤ ህገ ወጥ ተግባራትንም ፈጽመዋል የተባሉ ሰባት የውጭ አገር ዜጎች በ72 ሰዓታት ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ መሰጠቱ ይታወሳል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.