የሀገር ውስጥ ዜና

የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል እሴቱን በጠበቀ መልክ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ በሰላም ተጠናቋል-ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

By Tibebu Kebede

October 02, 2021

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገፃቸዉ መልእክት አስተላልፈዋል።

”የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከታችሁ የጸጥታ አካላት፣ የበዓሉ ታዳሚዎች እና የከተማችን ነዋሪዎች ምስጋና ይገባችኋል።

የከተማችን ነዋሪዎች ለበዓሉ ዝግጅት ከተማዋን በማስዋብ እና አካባቢን በማጽዳት እንዲሁም ለበዓሉ ታዳሚዎች ምግብ እና ውሃ በማቅረብ ያደረጋችሁት የትብብር እና የወንድማማችነት ተግባር እጅግ የሚደነቅ ነውም ብለዋል።

የዘንድሮው የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ፈጣሪን ከማመስገን ባለፈ ኢትዮጵያዊነትን በማጉላት የህዝቦችን አብሮነት፣ አንድነት እና ወንድማማችነትን ያጠናከረ በዓል ሆኗል።

በዓሉ የተለያዩ ብሄሮች እና ብሄረሰቦች በተለይም የጋሞ፣ የሀላባ፣ የሲዳማ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የተሳተፉበት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የተጠናከረበት በዓል ሆኖ አልፏል።

በነገው ዕለትም በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የሆራ አርሰዴ የኢሬቻ በዓል በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሁላችሁም የተለመደ ትብብራችሁን እንድታደርጉ እጠይቃለሁ ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!