የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ማራኪ በሆነ መልኩ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ላደረጋችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል- አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የምስጋና መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል የወንድማማችነት እሴት እና የኦሮሞን ህዝብ ትልቅነት ባሳየ መልኩ በሰላም በመጠናቀቁ ፈጣሪን በማመስገን የተሰማኝን ደስታ እገልጻለሁ ብለዋል።
ኤሬቻ የሰላም፣የእርቅና የይቅርታ፣ የአንድነትና የፍቅር በመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ ዛሬም ይህንኑ አስመስክሯል ብለዋል።
ይህ በዓል እንዲህ እንዲያምር እና ማራኪ በሆነ መልኩ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከምንም በላይ ባለቤት የሆነው የኦሮሞ ህዝብ የብሔር ብሄርሰቦች ወንድማማችነት እንዲጎለብት በማድረግ በዓሉ በጋራ እንዲከበር በማድረጋችሁ ምስጋና ይገባችኋል ነው ያሉት።
አባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄ በኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ተውባችሁ በሰላም መጥታችሁ አንድነታችሁን ጠብቃችሁ የሆራ ፊንፊኔን ኢሬቻ አሳክታችኋል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ፥ ፎሌዎች በጠንካራ አደረጃጀት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በወንድማማችነት መንፈስ፣ በዓል ለማክበር የመጡትን በፍቅር ስላስተናገዳችሁ፣ የሀገራችን ብሔር ብሄረሰቦች በዓሉ ላይ ታዳሚ በመሆን ለኦሮሞ ህዝብ ያላችሁን ክብር ስላሳያችሁ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።
በተለያየ ደረጃ የምትገኙ አመራሮች እና የጸጥታ የጸጥታ አካላት ብርድና ፀሐይ ሳይበግራችሁ ያለድካም እና ያለመሰልቸት በዓሉ እንዲሳካ አድረጋችሁ ለህዝብ ያላችሁን ወገንተኝተን በተጨባጭ በማስመስከራችሁ ምስጋና እና ክብር ይገባችኋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው።
እንዲሁም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ሚዲያዎች ይህንን ውብ በዓል ለአለም ህዝብ እና ጆሮ በማድረስ አኩሪ ተግባር በመፈጸማችሁ በራሴ እና በኦሮሚያ ክልል መንግስት ስም ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
ነገ ለሚከበረው ኢሬቻ ሆራ አርሰዴ እንደ ዛሬው ሆራ ፊንፊኔ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን