በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስምምነት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል- ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስምምነት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለፁ።
የስትራቴጂክ ጉዳዮች ተቋም የሚያዘጋጀው ወርሃዊ ሴሚናር ላይ በዛሬው እለት “በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተደረጉ ባሉ ድርድሮች” ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ሂደት፣ በሚሰጠው ጠቀሜታ እና በግድቡ ዙሪያ ከሱዳን እና ግብፅ ጋር እየተደረገ ስላለው ድርድር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የህዳሴ ግድብ ተርባይኖች ወደ 13 እንዲቀንሱ መደረጉን ተከትሎ ግድቡ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ሀይል እንደሚያመነጭ ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ይህም እስክ 210 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለመቆጠብ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከሀይል ማመንጨት በተጨማሪ ለአሳ ልማት እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ገልፀዋል።
ከግንባታ መዘግየት ጋር በተያያዘ የሀገር ውስጥ አቅምን ለመገንባት በሚል የአሌክትሮ መካኒካል ስራው ለሜቴክ መሰጠቱ ሀገሪቱን ዋጋ እንዳስከፈለ አንስተዋል፤ የምህንድስና ሳይንስ እና መልካም ፍላጎት ይለያያሉ ብለዋል።
ሜቴክ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ስራዎችን አለማከናወኑ፥ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ሀይልን ወደ ውጭ በመላክ ልታገኝ የምትችለውን እስከ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንድታጣ፣ የግንባታ ተቋራጩ ተጨማሪ ክፍያ እንዲጠይቅ፣ የተዘረጋው የሀይል ማስተላለፊያ መስመር ስራ እንዲፈታ እና ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ወደ ተወሳሰበ ድርድር እንድትገባ አድርጓታልም ነው ያሉት።
ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር እየተደረገ ስላለው ድርድር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ሲገልፁ፥ የህዳሴ ግድብ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።
ስለዚህም በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስምምነት ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለፁት።
በመድረኩ ላይ የተካፈሉ የፖሊሲ አውጭዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና አጥኚዎች በአጠቃላይ የግድቡ ሁኔታ እና በግድቡ ዙሪያ ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር እየተደረገ ባለው ድርድር ላይ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን ሰጥተው ውይይት ተደርጓል።
ከኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪዎች ቡድን ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው፣ አቶ ተፈራ በየነ እንዲሁም የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሙለታ መንገሻ