Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በ20 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የዓሳ ጫጩት ማስፈልፈያ ማዕከል ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሊገባ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በ20 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የአሳ ጫጩት ማስፈልፈያ ማዕከል ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የክልሉ የባህር የአሳ እና ሌሎች የውሃ ውስጥ አካላት ምርምር ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተዋበ እንዳሉት፥ በጣና ሃይቅ ላይ የሚስተዋለው የህገ ወጥ አሳ አስጋሪዎች እንቅስቃሴ የሃይቁን የአሣ ሃብት አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሶታል።

በአሳ የመራቢያ ወቅት ማስገር እና የእንቦጭ አረም መስፋፋትም ለአሳ ሃብቱ መመናመን ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።

እንዲሁም ከሆቴሎች እና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ወደ ሃይቁ የሚለቀቅ ፍሳሽ ቆሻሻ በአሳ ሃብቱ ላይ የተደቀነ ችግር መሆኑን አብራርተዋል።

የምርምር ማዕከሉ ከተቋቋመ ጀምሮ የአሳ መራቢያ ቦታዎች ልየታና ጫጩት የማስፈልፈል ስራ ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት ዳይሬክተሩ፥ የዘርፉ ችግሮች ተለይተው ለክልሉ የእንስሳት ኤጀንሲ መላካቸውን አስረድተዋል ።

አሁን ላይም ከግብርና ቢሮ በተገኘ 20 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የዓሳ ጫጩት ማስፈልፈያ ማዕከል ተጠናቆ በከፊል ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በዚህም 20 ሺህ 580 የዓሳ ጫጩቶች ተመርተው የተሰራጩ ሲሆን፥ 60 ሺህ የዓሳ ጫቹቶች ደግሞ በመመረት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ማዕከሉ በቅርቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባም ከ1 ሚሊየን እስከ 6 ሚሊየን የዓሳ ጫጩቶችን ያመርታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.