Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ ሀገራት ልዩ መልዕክተኞች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ጥር 28፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ልዩ መልዕክተኞች ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ ከአየርላንድ መንግስት ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኬኔት ቶምሰን እና ከፍልስጤም አስተዳደር ልዩ መልዕክተኛ እና የሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ዶክተር ናስሪ አቡጃሽ ጋር በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ከአየርላንድ መንግስት ልዩ መልዕከተኛ ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ ከአየርላንድ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ በተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አየርላንድ በኢትዮጵያ የምታካሂደውን የልማት ፕሮግራም አጠናክራ እንድትቀጥል እና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በስፋት ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሀገሪቱ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የአየርላንድ መንግስት ልዩ መልዕከተኛ አምባሳደር ኬኔት ቶምሰን በበኩላቸው፥ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ለቀጠናው እና ለአካባቢው ሰላም የምታደርገውን ጥረት ታደንቃለች ብለዋል።

አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል የገለጹት አምባሳደሩ፥ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ ሁኔታ የኢንቨስትመንት አውድ እንዲሰማሩ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ አቶ ገዱ ከፍልስጤም አስተዳደር ልዩ መልዕክተኛ እና የሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ዶክተር ናስሪ አቡጃሽ ጋር ባደረጉት ውይይት፥ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ እያካሄዱ ያሉትን ውይይት በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

አምባሳደር ዶክተር ናስሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን ሚና አድንቀዋል።

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብጽ እየተካሄደ ያለው ውይይት በሰላም እንደሚጠናቀቅ እምነታቸው መሆኑንም ገለጸዋል።

ፍልስጤም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል እየሰራች ነውም ብለዋል ልዩ መልዕክተኛው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.