የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት የአፍሪካ ኦስትሪያ የምርምር ጥምረት አባል ሆነ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት የአፍሪካ ኦስትሪያ የምርምር ጥምረት አባል መሆኑ ተገለጸ።
የአማራ ግብርና ምርምር በኦስትሪያ መንግስት የሳይንስና ትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ የተመሰረተው የአፍሪካ ኦስትሪያ የምርምር ጥምረት መረብ አባል ሆኗል።
ጥምረቱ 63 የአፍሪካና 18 የኦስትሪያ ዩኒቨርሲቲዎችንና የምርምር ተቋማትን ያካተተ ሲሆን፥ በአፍሪካ እና በኦስትሪያ ዩኒቨርሲዎች እና የምርምር ተቋማት መካከል የምርምርና የስልጠና ትብብሮችን ያጠናክራል ተብሏል።
በተጨማሪም የጋራ የምርምር አጀንዳዎችን በመቅረጽ፣ ለምርምር ስራዎች የሚያስፈልግ ሀብት በማፈላለግ እና የጥምረቱ አባል በሆኑ የትምህርትና የምርምር ተቋማት መካከል የተማሪዎችና የተመራማሪዎችን ዝውውር ያጠናክራል።
ጥምረቱም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያስቀመጠውን የዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካት ያለመ መሆኑን ከአማራ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።