Fana: At a Speed of Life!

ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ለተፈናቀሉ ወገኖች ገቢ ማሰባሰቢያ ግጥሚያ አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ መሰከረም 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚውል ፋሲል ከነማና የኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ቡድኖች ጨዋታ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተካሄደ።

በወዳጅነት ጨዋታውም ፋሲል ከነማ ኢትዮጰያ ቡናን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በዕለቱ እንደተናገሩት ፥ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት በጎ ፈቃደኞች እያደረጉ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።

ይህ የበጎነት ተግባርና የሰብዓዊ ድጋፍ ትልቅ የህሊና ስንቅ ከመሆኑም በላይ በአስቸጋሪ ወቅት ወገን ለወገን ያለውን መረዳዳት በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ያስችል ዘንድም ገቢ ማሰብሰቢያ ፕሮግራሞች በስፋት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌደሬሽን ፀሃፊ እና የውድድሩ አዘጋጅ አቶ መኳንንት ደነቀው በበኩላቸው ፥ አሸባሪው የህውሓት ቡድን በአማራ ክልል በፈፀመው ወረራ ዘርፈ ብዙ ጉዳት አድርሷል።

በዚህም ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ መንግስትና ህብረተሰቡ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለማገዝም የአማራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት የገቢ ማሰባሰቢያ ስፖርታዊ ውድድሩ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

የዛሬውን ጨምሮ በቀጣይ በሚደረጉ የስፖርታዊ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ገልጸዋል።

የፊታችን እሁድ የአዲስ አበባ የሲቲ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንዲካሄድ የተወሰነ መሆኑን ጠቅሰው÷ የባህር ዳር ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ጨዋታውን በመታደም አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ጨዋታ ሰብዓዊነትን ዓላማ ያደረገ በመሆኑ ሁለቱም ቡድኖች አሸናፊ እንደሚሆኑ ጠቅሰው÷ ለቡድኖች ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም የእግር ኳስ ግጥሚያ እና የሩጫ ውድድሮች እንደሚካሄዱ አመልክተዋል።

የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን አምበል አምሳሉ ጥላሁን በበኩሉ ፥ ጨዋታው ለተፈናቀሉ ወገኖች ገቢ ማሰባሰቢያ በመሆኑ እንዳስደሰተው ገልጿል።

ለዚህ በጎ ዓላማ በስታዲም በመታደም ጨዋታውን የተመለከቱ ደጋፊዎችን አመስግኖ÷ ሌሎች የእግር ኳስ ክለቦችም በመሰል የበጎ ተግባር ዓላማ እንዲሳተፉ ጠይቋል።

የኢትዮጰያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ሃይሌ ገብረተንሳይ እንዲሁ በሰጠው አስተያየት በዚህ የበጎ ተግባር ስራ ለሚውለው የእግር ኳስ ጨዋታ በመሳተፍ ኩራት እንደተሰማው መናገሩን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.