መኪና አስመጣላሁ በሚል ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ከሰዎች ሰብስቦ ተሰወረ የተባለው ኩባንያ ምላሽ ሰጥቷል
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) መኪና አስመጣላሁ በሚል ከግለሰብ 173 ሺህ ብር በላይ በድምሩ ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ሰብስቦ ተሰወረ የተባለው ኩባንያ አለሁ ብሏል።
ፋት ትራንስፖርት ቴክኖሎጂስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አሽከርካሪውን ጨምሮ 5 ሰዎችን የሚያሳፍር መኪና፣ በ30 በመቶ ቅድመ ክፍያ በ90 ቀናት ውስጥ አስረክባለሁ በማለት ከ102 ሰዎች ገንዘብ ተቀብሎ መሰወሩን ቅሬታ አቅራቢዎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በቅድመ ክፍያ የተጠየቀውን ገንዘብ ከፍለው፣ በውላቸው መሰረት ተሽከርካሪዎችን ያላገኙና ድርጅቱ ከአድራሻው ተሰወረብን ያሉ ባለጉዳዮችን ቅሬታ ባሳለፍነው ማክሰኞ ዕለት መዘገቡ ይታወሳል።
ዘገባውን ተከትሎም ፋት ትራንስፖርት ቴክኖሎጂስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት አቶ ዳግም ግዛቸው እና የንግድ ፈቃድ በስማቸው ያለው ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ጣቢያችን ተገኝተው ምላሽ ሰጥተዋል።
የድርጅቱ የስራ ሃላፊዎች በምላሻቸውም ደንበኞቻችን ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢ ቢሆንም በአድራሻችን እንዳንገኝ ያደረጉን እነርሱ ናቸው ይላሉ።
ድርጅቱ ከውል ሰጭ ደንበኞቹ፣ በተቀበለው ውል መሰረት በ4 ዓመት ጊዜ የሚከፈል የ70 በመቶ ማለትም ለእያንዳንዱ ተሽከርካሪ 404 ሺህ 250 ብር፣ በብድር ማመቻቸቱን ውሉ ላይ ሰፍሯል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከዚህ በፊት በሰራው ዘገባ ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ በውላችን መሰረት ብድር አመቻቻለሁ ያለው ድርጅት ሂደቱን እንኳን ሳያስጀምር ጠፋብን ብለው ነበር።
የፋት ሃላፊዎች በበኩላቸው በሃገሪቱ ላይ የተስተዋለው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት በ90 ቀናት የባንክ ሂደቱን መጨረስ አልቻልንም ነበር ይላሉ።
በአንፃሩ ቅሬታ አቅራቢዎች ድርጅቱ የባንክ ሂደቱን በአፋጣኝ አለመጀመሩና ከጀመረም በኋላ የተባለው የገንዘብ እጥረት ከመከሰቱ አስቀድሞ የባንክ ሂደቱን እንዲጨርስ ከባንክ ሳይቀር ጥሪ ቀርቦለት ለማስፈጸም ፈቃደኛ እንዳልነበር አንስተዋል።
ፋት ትራንስፖርት ቴክኖሎጂስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ባሰረው ውል መሰረት ካለቅድመ-ሁኔታ ገንዘብ የመመለስ ግዴታውን እየተወጣ አለመሆኑንም ባለጉዳዮች ተናግረዋል።
የስራ ሃላፊዎቹ ጉዳዩን አስመልከተው በሰጡት ምለሽ፥ ድርጅቱ ገንዘባቸው እንዲመለስ የጠየቁ የሰባት ደንበኞቻቸው ገንዘብ ተመላሽ መደረጉን አብራርተዋል።
ይሁን እንጂ ከመኪና አስመጪ ድርጅቶች ጋር ገንዘብ ከፍለው ውል በመግባታቸው ምክንያት ገንዘብ የመመለስ ሂደቱ መጓተቱን የስራ ሃላፊዎች አስረድተዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎች፤ በውላችን መሰረት በግል አልያም በህብረት ውላችንን አፍርሰን ገንዘባችን እንዲመለስ የመጠየቅ መብት አለን ብለዋል።
በውሉ መሰረት ገንዘባቸው እንዲመለስ ለጠየቁ ከ20 በላይ ግለሰቦች ገንዘብ ሳይመልስ መቆየቱን ያነሱት የስራ ሃላፊዎቹ፥ ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆኑ የገንዘብ ምላሽ ደብዳቤዎችን አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ገንዘብ ተመላሽ ተደርጎላቸዋል ከተባሉት ደንበኞች ውስጥ የሁለቱ በህግ ወጥ የክፍያ ስርዓት ሊፈጸም የነበረ በመሆኑ ጉዳዩ በህግ መያዙን ቅሬታ አቅራቢዎች ይናገራሉ።
ኤፍ ቢ ሲ ከዚህ ቀደም በሰራው ዘገባ ፋት ትራንስፖርት ቴክኖሎጂስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፤ በወይዘሮ ፍቅርተ መኮንን ይርጋ፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07፤ በሃገር ውስጥ ንግድ ረዳት ዘርፍ በህጋዊነት በተመዘገበ የንግድ ፈቃድ እንደቆየ አረጋግጧል።
ድርጅቱ ባሳለፍነው ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓመተ ምህረት የንግድ ፈቃድ ማሻሻያ በማድረግ ስራ አስኪያጁን በአቶ ዮሴፍ ተስፋዬ መንግስቱ ቀይሯል።
ይሁን እንጂ ድርጅቱ የ2012 ዓመተ ምህረት የስራ ፈቃዱን ያላሳደሰ መሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አረጋግጧል።
አቶ ዮሴፍ በቀጣይ ፋት ትራንስፖርት ቴክኖሎጂስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፤ ሰው አልባ ሆኖ የሰነበተው ቢሮውን በመክፈት ለደንበኞቹ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በርስቴ ጸጋዬ