የዳያስፖራ አባላቱ አውሮፓ ሕብረት ያቀረበውን ረቂቅ ውሳኔዎች እንዲያጤነው ጠየቁ
አዲስ አባባ፣ መስከረም 28፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በጀርመን የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈዉን ረቂቅ ውሳኔ እንደገና እንዲያጤነው ጠየቁ፡፡
በጀርመን የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት÷ በትግራይ የሰብዓዊ ሁኔታን በተመለከተ እና ከኢትዮጵያ መንግስት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ታያይዞ የአዉሮፓ ሕብረት ያሳለፋቸዉን የውሳኔ ሃሳቦች እንደገና ሊያጤነው ይገባል ሲሉ በደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡
የአዉሮፓ ሕብረት የተመለከታቸዉ ረቂቅ ውሳኔዎች ትክክል አለመሆናቸዉንና የዳያስፖራ አባላቱ እንደማይስማሙባቸዉ በደብዳቤ ገልጸዋል።
በአፋርና በአማራ ክልሎች እየተፈጸመ ያለውን ግፍና የንፁሃን ዜጎች ግድያ ሆን ብሎ ችላ በማለት÷ በአንፃሩ በትግራይ ያለዉን የሰብዓዊ መብትበተመለከተ ሕብረቱ መወያየቱ ፍትሃዊ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከሰተዉ ሰብዓዊ ቀዉስ በአንድ ክልል ላይ ብቻ አለመሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ገበሬዎች ወቅታዊ የእርሻ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ለመርዳትና በክልሉ ያለውን ሰብዓዊ ሁኔታ ከግምት ዉስጥ በማስገባት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጉን እና የኢትዮጵያ ወታደሮች አካባቢውን ለቀው የወጡበትን የጊዜ ክፍተት በመጠቀም አሸባሪው ቡድን ጥቃት አድርሷል፡፡
በዚህም በአፋርና አማራ ክልሎች ጥቃት በመሰንዘር መንደሮችንና መሠረተ ልማቶችን አውድሟል፤ የንፁሃንን ህይወትም ቀጥፏል ነው ያሉት የዳያስፖራ አባላቱ፡፡
አሁንም የሽብር ቡድኑ በአጎራባች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሕፃናትን ጨምሮ የጅምላ ምልመላውን ቀጥሎ÷ ጦርነቱን ለማስቀጠል እንደወሰነ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ ሕብረቱ÷ በረቂቅ ውሳኔው ውስጥ ስለዚህ እውነታ አለመጥቀሱን የዲያስፖራ አባላቱ ገልጸዋል፡፡
ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር በተሳሳተ መንገድ መገለፁንም ነው የጠቆሙት አባላቱ፡፡
በሃገሪቱ በተካሄደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ÷ አገራዊ የፖለቲካ ውይይትን ለማስቀጠል እየተደረገ ባለው ጥረት በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንግስት መመረጡን በደብዳቤያቸዉ ማመላከታቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!