Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና አልጄሪያ በትምህርት ዘርፍ በትብብር ለመስራት ውይይት አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና አልጄሪያ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የሚያደርጉትን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ የሁለቱ ሃገራት የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ውይይት አድርገዋል።
በአልጀሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት የሁለቱም ሃገራት የትምህርት ሚንስቴር ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
ኢትዮጵያና አልጄሪያ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ አቅም ግንባታ፣ በስልጠናና የጋራ ምርምር ስራዎች ላይ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው እንደገለጹት÷ በአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የሚደረጉ ትብብሮች በሀገሮች መካከል በልማቱ ዘርፍ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥና ፓን አፍሪካኒዝምን የበለጠ ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡
በኢትዮጵያና በአልጄሪያ መካከል በስልጠና፣ በትምህርት፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ያሉ የተሻሉ አሰራሮችን መለዋወጥ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ÷ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የሚደረጉ ትብብሮች የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ በመምህራንና ተማሪዎች ልውውጥ አቅም ለመገንባት፣ የመማር ማስተማር ልምድ ልውውጥ ለማድረግ ሁኔታዎችን ያመቻቸ ውይይት ነው ብለዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል በበኩላው÷ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል ከአልጄሪያ ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁነት አለ ብለዋ፡፡
በአልጄሪያ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክተር አፈስኪ ሳይዳኒ እንደገለጹት÷ ከኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት፣ የሁለቱ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች የሚያደርጉትን ጉድኝት ለማጠናከርና እርስ በእርስ ያላቸውን ትስስር ለማጎልበት አልጄሪያ ዝግጁ ናት፡፡
ለትብብሩ ተግባራዊነት በቅርቡ የረቂቅ መግባቢያ ሰነድ ልውውጥ እንደሚደረግ ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ እ.ኤ.አ በ2014 የሳይንስና ቴክኖሎጂ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን በአልጀሪያ ከኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.