በምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ድጋፍ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ።
በአካባቢው የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መከላከል ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት እና ገለፃ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይም የተለያዩ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ የዓለም የምግብ እና የግብርና ድርጅት (ፋኦ) ተወካዮች እንዲሁም ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በዚህም የበረሃ አንበጣ መንጋ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እያደረሰ ባለው ጉዳት ዙሪያ ገለፃ የተደረገ ሲሆን፥ በተለይም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በአንበጣ መንጋው በጣም የተጎዱ ሀገራት መሆናቸው ተጠቅሷል።
የበረሃ አንበጣ ከሶስቱ ሀገራት በተጨማሪም በኤርትራ እና በሱዳን ላይ መጠነኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም ተብራርቷል።
የበረሃ አንበጣ መንጋው እንቅስቃሴ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚያደርገው ወረራ ቀጣይነት ያለው ነው የተባለ ሲሆን፥ በኢትዮጵያን በአውሮፓውያኑ እስከ ሰኔ 2020 ድረስ ሊቆይ ይችላል ነው የተባለው።
በሀገራቱ ላይ በአንበጣ መንጋ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስም ዓለም አቀፍ የልማት አጋር የሆኑ ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በመድረኩ ላይ ጥሪ ቀርቧል።
የዓለም የምግብ እና የግብርና ድርጅት (ፋኦ) በመድረኩ ላይ፥ የበረሃ አንበጣ መንጋ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በአፋጣም ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብሏል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ የዓለም የምግብ እና የግብርና ድርጅት (ፋኦ) እስካሁን ላደረገው ድጋፍ አመስግና፥ የአንበጣ መንጋው እስኪጠፋ ድረስ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጠይቃለች።
የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በአፋር፣ ሰሜን ምስራቅ አማራ፣ ደቡብ ትግራይ፣ ምስራቃዊ ሶማሌ እና ኦሮሚያ፣ ምእራብ እና ምስራቅ ሀረርጌን ጨምሮ እስከ ድሬዳዋ ድረሰ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል።
አሁን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የባሌ፣ ቦረና እና ጉጂ ቆላማ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል በመስፋፋት ሌላ ስጋት ፈጥሯል።
በምስክር ስናፍቅ