መንግሥት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰሜን ወሎና በጎንደር ለሚኖሩ ወገኖች ተገቢው ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪውን አቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰሜን ወሎና በጎንደር ለሚኖሩ ወገኖች ተገቢው ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቃታዊ ጉዳይን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫውም ህወሓት በሰሜን ወሎና ጎንደር የሰው ህይወት ማጥፋቱን እና መሠረተ ልማቶችን ማውደሙን አንስቷል፡፡
አሸባሪው ቡድን ሰዎችን በፍርሃት እና በማስገደድ የፖለቲካ ስልጣኑን ለመያዝ አደገኛ ተግባሩን መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመራ የነበረው ይህ ቡድን በትግራይ አሁንም በሴፍቲኔት ፕሮግራም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ እንዳለ መግለጫው ጠቅሶ÷ ይህም ለትግራይ ሕዝብ ፍፁም ደንታ እንዳልነበረው ማሳያ ነው ብሏል፡፡
በተጨማሪም ወረራ ባደረገባቸው በሰሜን ጎንደርና በሰሜን ወሎ አካባቢዎች የመንግሥትን የገለልተኛ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማቃለያን በመቃወም ÷ ሕወሓት ለአማራ ሕዝብ ያለውን ጠላትነት በድጋሚ አረጋግጧል፡፡
ቡድኑ የብዙ ቤተሰቦችን ሕይወት ለማበላሸት ያለመ መሆኑን ወርሮ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በቅርቡ በአሸባሪው ተይዘው የነበሩ አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች እንደገለጹትም÷ የአሸባሪው ህወሓት ወታደሮችና ተባባሪዎቻቸው የአርሶ ደሩን ሰብልና ሌሎች ንብረቶች ዘርፈዋል ፤ አውድመዋል፡፡
ከዚህ የከፋው ደግሞ የአርሶ አደሮችን የተከማቸ ምግብ መውሰዳቸውና ቀሪውንም ማውደማቸው ነውም ይላል ሚኒስቴሩ በመግለጫው፡፡
ባደረሰው ውድመትም ÷ የምግብ እርዳታ መጋዘኖች እንኳን አልቀሩትም ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ከሚገኙ ተረጂዎች የተከፋፈለ ዕርዳታንም ወስዷል ነው የተባለው፡፡
በኢትዮጵያ የአርሶ አደሮች ኑሮ በእንስሳት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያነሳው መግለጫው÷ በሚያሳዝን ሁኔታ እነዚህም ከወያኔ የጥፋት ተግባራት አልተረፉም ብሏል፡፡
አሸባሪው ቡድን የግለሰቦች ሕይወትን ከማጥፋት አልፎ ማህበረሰብ ላይ ጥቃት መፈጸሙ እና ህይዎት ማጥፋቱም ነው የተገለጸው፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች አጥፊው ቡድን የእንክብካቤ ማዕከላትን ፣ ትምህርት ቤቶችን ፣ ኮሌጆችን ፣ ባንኮችን ፣ ጤና ጣቢያዎችን ፣ ሆቴሎችን እና ሌሎች ተቋማትም አልቀረውም፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን እየተሰራ የነበረው የአዋሽ ወልዲያ – ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት በሚያሳዝን ሁኔታ በዚህ ኃላፊነት የጎደለው ቡድን ኢላማ መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡
እነዚህ የወያኔ ድርጊቶች ለትግራይ ህዝብ ኑሮ መሻሻል አስተዋፅኦ አይኖራቸውም ፤ ይልቁንም በህዝቦች መካከልጥላቻን እና ቂምን እንደሚፈጥር መግለጫው አመላክቷል፡፡
በወሎና በጎንደር ህወሓት የፈጸመው፤ አሁንም እየፈጸመ ያለው ግፍና በደል በስልጣን ለመቆየት እንደየመጨረሻ ሙከራ ብቻ ለማድረግ እንደሆነ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
በመጨረሻም በጁንታው ለተጎዱ ዜጎች ሁሉ የተፋጠነ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲደረግለት በተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀረበው የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰሜን ወሎ እና በጎንደር ለሚኖሩ ወገኖች ችግርና ፍላጎት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!