Fana: At a Speed of Life!

በምዕራብ ጎንደር ቋራ ወረዳ በአኩሪ አተር ሰብል ምርት የገበያ ትስስር ተፈጠረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ የንግድ ድርጅቶች በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች በአኩሪ አተር ሰብል ምርት የገበያ ትስስር መፍጠራቸውን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ።
የነጭ ወርቅ ምድር ከሚባሉ አካባቢዎች ውስጥ በአማራ ክልል የሚገኘው ምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። በዞኑ እንደ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ ማሽላ እና አኩሪ አተር በብዛትይመረታል፡፡ በሀገሪቱ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ከሚሆኑ ምርቶችም አንዱ አኩሪ አተር ነው፡፡
ምርቱ ለኢንዱስትሪዎች ሰፊ ግብዓት እንዲፈጥር እና አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑም በአሥር የንግድ ድርጅቶችና በአምራቹ መካከል የገበያ ትስስር ተፈጥሯል።
በአኩሪ አተር ሰብል የገበያ ትስስር መፈጠሩ ከአሁን በፊት ይደርስባቸው የነበረውን የገበያ አሻጥር ከመቅረፉ ባሻገር፥ ምርቱን በስፋትና በጥራት ማምረት እንዲችሉ የሚያበረታታ እንደሆነ አርሶ አደር ጌትነት አብዬ እና አሰፋ ጫኔ ለአሚኮ ተናግረዋል።
መንግሥት እና የንግድ ድርጅቶች በጋራ በመሆን ድካምን የሚቀንስ የአኩሪ አተር መፈልፈያ ዘመናዊ ማሽን እንዲያቀርቡላቸውም የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው ባለሀብቶችና አርሶአደሮች ጠይቀዋል፡፡
በዞኑ በግብርናው መስክ ለተሰማሩ ባለሀብቶችና አርሶአደሮች ከወለድ ነጻ የሆነ የብድር አገልግሎት በመስጠት እና አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት አምራቾች ምርታቸውን በፈለጉት ጊዜ እንዲሸጡላቸው የጋራ ውል በመውሰድ የገበያ ትስስር መፍጠራቸውንም የንግድ ድርጅት ተወካዮች ተናግረዋል።
በምርት ዘመኑ በወረዳው 23 ሺህ 557 ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ሰብል ልማት መሸፈኑን የተናገሩት የቋራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሰውመሆን ሽታው፥ 4 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በክላስተር መልማቱን ነው የገለጹት፡፡
በአርሶ አደሮች እና በንግድ ድርጅቶች መካከል የገበያ ትስስር መፈጠሩ÷ አርሶ አደሮች ይደርስባቸው የነበረውን የገበያ አሻጥር የሚያስቀር እና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የቋራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤፍሬም ወርቁ እንደተናገሩት፥ በምርት ዘመኑ ከ10 ያላነሱ የንግድ ድርጅቶች በወረዳው ገብተው በእርሻ ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ባለሀብቶች እና አርሶአደሮች ጋር በአኩሪ አተር ሰብል ምርት የሥራ ውል ገብተዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.