ዓለምአቀፋዊ ዜና

በራችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ክፍት ነው – ቻይና

By Alemayehu Geremew

October 15, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሯ እንደማይዘጋ፣ ይልቁንም የበለጠ ክፍት እንደሚሆን አስታወቀች፡፡

የቻይና ፕሬዚዳንት ቺ  ጂንፒንግ÷ ቻይና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሯ ሁልጊዜም ክፍት እንደሆነ በ2ኛው የተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፉ ዘላቂ የትራንስፖርት ኮንፈረንስ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ÷በወረርሽኙ ምክንያት በክፍለ ዘመናችን አይተን የማናውቃቸው ጉልህ ለውጦች ቢከሰቱም የዓለም እድገት እንዲሁም እየዘመነ የመጣው ዓለም አቀፋዊ የትራንስፖርት ትብብር ይለመልማል ብለዋል፡፡

በቀጣይም በመሠረተ ልማት ትስስር ፣ ባልተገደበ የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲሁም በሥልጣኔዎች መካከል በሚደረጉ ሁለንተናዊ ግንኙነቶች አዲስ ምዕራፍ እንጽፋለን ነው ያሉት – ቺ ጂንፒንግ፡፡

ቺ – አክለውም ትራንስፖርት የኢኮኖሚ ደም ስር ነው ብለው÷ በሥልጣኔዎች መካከል ትስስር እንዲቀጥልና ዓለም እንደ አንድ መንደር እንድትቀራረብ የሚያስችል ዘርፍ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ቺ – በንግግራቸው ÷ የትራንስፖርቱ ዘርፍ እያደገ መምጣቱን ታሪክ አጣቅሰው አንስተዋል፤ በዘመናዊው ዓለምም የትራንስፖርቱ ዘርፍ እድገት ለኢኮኖሚ ትስስር እና ለህዝቦች ግንኙነት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ የዘገበው ሲጂቲ ኤን ነው፡፡

በዓለማየሁ ገረመው