አቶ ገዱ ከተለያዩ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ጎን ለጎን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻቸው ማሪ ቱምባ ንዜዛ እና ከታንዛኒያ አቻቸው ፕሮፌሰር ፓላማ ጋምባ ጆን ካቡዲ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው በሁለትዮሽ፣ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ከዚህ ባለፈም የአባይ ተፋሰስ አባል ሃገራትን ህዝቦች እያደገ የመጣ የመልማት ፍላጎት ማሟላት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ በውይይታቸው መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪ ቱምባ ንዜዛ ጋር በነበራቸው ውይይት ሁለቱ ሃገራት ያላቸውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
ሚኒስትሮቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮንጎ የሚያደርገውን በረራ እያደገ ከመጣው የተጓዥ ቁጥር ጋር ማጣጣም እንዲችል ተጨማሪ ትብብር እና ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተወያይተዋል።
በተመሳሳይ አቶ ገዱ ከታንዛኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፓላማጋምባ ጆን ካቡዲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ማካሄድ እና ከናይል ተፋሰስ ጋር በተያያዘ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
የታንዛኒያ መንግስት በሃገሪቱ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እያደረገ ላለው ድጋፍና በቅርቡ ለኢትዮጵያ ኤምባሲ መገንቢያ የሚውል መሬት በማቅረቡ ምስጋና አቅርበዋል።
የታንዛኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፓላማጋምባ ጆን ካቡዲ በበኩላቸው፥ ሃገራቱ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው ይህን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አቶ ገዱ ለሚኒስትሮቹ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ እያካሄዱት ያለውን ድርድር በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በተያያዘም ሚኒስትሩ ከናይጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆፍሪ ጂዶፎር ክውስኪ ኦንይማ እና ከቡሩንዲው የውጭ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢዘችይል ኒቢጊራ ጋር በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትብብር ዙሪያ መክረዋል።
ከናይጀሪያው አቻቸው ጋር በነበራቸው ውይይት የሃገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መከናወን ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።
ከቡሩንዲው የውጭ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ባደረጉት ቆይታም ከናይል ውሃ አጠቃቀም፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የሃገራቱን ግንኙነቱን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision