Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል በሸካና ቤንች ሸኮ ዞኖች የተፈጠረውን  የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል በሸካ እና ቤንች ሸኮ ዞኖች የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ  እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጸው፥ ባለፉት 2 ሳምንታት ቴፒ ከተማን ጨምሮ በተፈጠረው ግጭት የ7 ሰዎች ህይወት አልፏል።

ግጭቱ በአካባቢው የመዋቅር አደረጃጀት ጥያቄን ወደ ግጭት ለመውሰድ በሞከሩ የተደራጁ ቡድኖች የተፈጠረ ስለመሆኑም ገልጿል።

ከአንድ አመት ወዲህ በአካባቢው ተደጋጋሚ ግጭቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል።

የክልሉ ፀጥታ በኮማንድ ፖስት ስር እንዲጠበቅ ከመደረጉ አስቀድሞም ይህን ግጭት ለማርገብ ያለመ የፀጥታ ሀይል ቁጥጥር መጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ስራ መጀመሩም ይታወሳል።

ሆኖም የተረጋጋ እየመሰለ አልፎ አልፎ በሚከሰት ግጭት የአካባቢው ፀጥታ ታውኳል።

የደቡብ ክልል የጸጥታና አስተዳደር ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፥ በሸካ ዞን እና በቤንች ሸኮ ዞን የሚከሰተው አለመረጋጋት ምክንያቱ የመዋቅር ጥያቄ ነው።

ይሁን እንጅ ከውይይት ይልቅ ግጭትን በመረጡ የተደራጁ ቡድኖች ችግሩ መፈጠሩንም አውስተዋል።

በሁለቱ ዞኖች በተለይም ከሸካ ዞን ቴፒ ከተማ እና በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ዳግም የፀጥታ ችግሩ ማገርሸቱን ገልጸዋል።

የህዝቡን ጥያቄ ለግጭት መንስኤ ያደረጉ ሀይሎች መንገድ መዝጋት እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን እንዲዘጉ የማስገደድ ተግባር ፈጽመዋልም ነው የሚሉት።

የፌደራልና የክልሉ የጸጥታ ሀይልም አካባቢውን ለማረጋጋት እየሰሩ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህ የፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና በወንጀል የተጠረጠሩ አካላትን ለመያዝ በተደረገ ጥረት የፀጥታ ሀይል አባልን ጨምሮ 7 ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል።

ምክትል የቢሮ ሀላፊው ትክክለኛውን የህዝቡን የመዋቅር አደረጃጀት ጥያቄ በውይይት ለመፍታት የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ ሆን ብለው አካባቢው እንዳይረጋጋ የሚሰሩ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።

እስካሁን 68 ተጠርጣሪዎች ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት በማድረግ በወንጀል የተጠረጠሩትን በህግ ፣ እርቅ የፈጸሙትን ደግሞ ወደ ህብረተሰቡ የመቀላቀል ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቴፒ ከተማ ከትናንት ጀምሮ አንጻራዊ ሰላም እየታየ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ሃላፊው፥ ዞኖቹን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ ከህዝቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

አስተያየታቸውን ለጣቢያችን የሰጡ የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች ባለፉት ሁለት ቀናት አንጻራዊ ሰላም በከተማዋ እየታየ መሆኑን ነግረውናል።

መንግስትም በዘላቂነት ህግ እና ስርዓትን በማስከበር ለመዋቅር ጥያቄው ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጢሞቲዎስ ሙሉጌታ በኩላቸው፥ ከፀጥታ ችግሩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት በህግ ጥላ ስር ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከተማዋን በተሻለ ለማረጋጋትም ከህዝቡ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሀይለእየሱስ መኮንን

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.