ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባል ሆነው ተመረጡ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባላት ሆነው ተመረጡ።
ሁለቱ ሃገራት ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የምክር ቤቱ አባል ሆነው እንደሚያገለግሉ ተገልጿል።
የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤቱ የአፍሪካ ህብረት ግጭት መከላከል፣ መቆጣጠር እና አፈታት ላይ ውሳኔ ሰጭ አካል ነው።
ከዚህ ባለፈም በአፍሪካ ለሚከሰቱ ግጭቶች እና ቀውሶች ወቅታዊ እና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የደህንነት እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ተቋም ነው።
ይህም በአፍሪካ ሰላምና ፀጥታን ለማስከበር ለሚሰራው ተቋም ምሰሶ ያደርገዋል ነው የተባለው።
ምክር ቤቱ እኩል ድምፅ ያላቸው 15 አባላት ያሉት ሲሆን፥ አምስት አባላት ለሶስት ዓመት እንዲሁም 10 አባላት ደግሞ ለሁለት ዓመታት ያስመርጣል።
ሁሉም አባላት በአፍሪካ ህብረት ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ሲመረጡ፥ በአፍሪካ ህብረት መደበኛ ስብሰባ አባልነታቸው ይፀድቃል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision