የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የቀይ ሽንኩርት ምርቶች በቀጥታ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው ተባለ

By Meseret Awoke

October 20, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ለህብረተሰቡ ምቹ ናቸው ተብለው በተመረጡ 19 ስፍራዎች ወደ ከተማዋ የገቡ የቀይ ሽንኩርት ምርቶች በቀጥታ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታወቀ ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ጌታቸው እንደገለጹት÷ በትናንትናው እለት ከኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የገቡ የቀይ ሽንኩርት ምርቶች በቀጣይ ቀናትም የሚገቡ ምርቶች ማህበራቱ በመደበኛነት ከሚሸጡባቸው የግብይት ስፍራዎች በተጨማሪ ለህብረተሰቡ ምቹ ናቸው ተብለው በተመረጡ ስፍራዎች እየቀረቡ ነው፡፡

በዚህም በአራት ኪሎ አደባባይ፣ ስድስት ኪሎ አደባባይ፣ ፈረንሳይ አካባቢ /አደባባይ/፣ ሽሮሜዳ አካባቢ/ አደባባይ/፣አዲሱ ገበያ አካባቢ/ አደባባይ /፣ፒያሳ ጊዮርጊስ አካባቢ/ማዘጋጃ ቤት ፊትለፊት /፣ አዲስ ከተማ አካባቢ /መርካቶ/፣ ዊንጌት አካባቢ /አደባባይ/፣ ጦር ሀይሎች አካባቢ/አደባባይ/፣ ኮልፌ አስራ ስምንት ማዞሪያ፣ አለርት ሆስፒታል አካባቢ፣ አየርጤና አካባቢ /አደባባይ/፣ ጀሞ አካባቢ /አደባባይ/፣ አቃቂ ቃሊቲ /መናህሪያ አካባቢ/፣ ቦሌ መገናኛ አደባባይ፣ ሀያ ሁለት ጎላጎል ህንጻ አካባቢ/አደባባይ/፣ የረር አደባባይ፣ ሜክሲኮ አደባባይ፣ የካ አባዶ፣ ሀያት አደባባይ አካባቢዎች ምርቶቹ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡

ምርቶቹን ለህብረተሰቡ በቀጥታ እንዲያቀርቡ በከተማ አስተዳደሩ በጊዜያዊነት ተፈቅዶላቸው ከማህበራቱ ጋር መግባባት ላይ በመደረሱም ከዛሬ ጀምሮ ማህበራቱ ወደ ግብይት እያከናወኑ መሆናቸውን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በማህበራቱ በኩል ሌሎችም የግብርና ምርቶች በቀጥታ ከአምራች የህብረት ስራ ማበራት ጋር በሚደረግ ፈጣን የገበያ ትስስር በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አቶ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡

በጋዲሳ ጌታቸው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!