Fana: At a Speed of Life!

እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት መከላከል ካልተቻለ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት መከላከል ካልተቻለ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ሲሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንተነህ ተስፋዬ አሳስቡ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የማህበራዊ ሚዲያ የሳይበር ተጋላጭነትና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች፣ የአይሲቲ ባለሙያዎችና ለባለድርሻ አካላት ስልጠና እየሰጠ ነው።

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እ.ኤ.አ በ2020 በተሰነዘረባቸው የሳይበር ጥቃት 94 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠማቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታውቋል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንተነህ ተስፋዬ ሁለተኛው የሳይበር ደህንነት ሳምንት በተዘጋጀው ስልጠና ባደረጉት ንግግር ÷ መገናኛ ብዙሃን በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ዘርፎች አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም የምርመራ ጋዜጠኝነትን የሚያከናውኑ በመሆናቸው ለሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ መሆናቸውን አንስተው÷ ስልጠናው በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመግታት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በሳይበር ጥቃት ዓለም እ.ኤ.አ በ2020 ብቻ 2 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ መድረሱን እንደአብነት አንስተዋል።

ስለሆነም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት መከላከል ካልተቻለ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ሲሉም አሳስበዋል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አዘጋጅነት “የሳይበር ደህንነት የጋራ ሃላፊነት! እንወቅ፣ እንጠንቀቅ!” በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 1 ጀምሮ መከበር መጀምሩ የሚታወቅ ነው።

የሳይበር ደህንነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ ሲከበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ እየተከበረ መሆኑን ኢፕድ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.