ክልሉ በቦረና ዞን የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል 30 ሚሊየን ብር መደበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ለመከላከል እንዲቻል የክልሉ መንግሥት 30 ሚሊየን ብር መመደቡን የኦሮሚያ ክልል አደጋና ስጋት ኮሚሽን ገለፀ ።
የክልሉ አደጋ ስጋት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ገረሙ ኦሊቃ ለኢፕድ እንደገለፁት÷ በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ነው።
ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳብራሩትም÷ በአሁኑ ወቅት ድርቅ በቦረና ዞን የምግብና የውሃ እጥረት አስከትሏል።
የተከሰተው ችግርም በሰውና በእንስሳት ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ለእንስሳት መኖ 10 ሚሊየን ብር እንዲሁም ለአደጋው ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እርዳታ የሚውል 20 ሚሊየን ብር በክልሉ መንግሥት አማካኝነት ተመድቧል።
15 የውሃ ቦቴዎችም በቋሚነት ተመድበው የውሃ ችግሩን ለመቅረፍ ሥራ ጀምረዋል ።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለፃ÷ በመስከረም ወር አጋማሽ በአካባቢው ይዘንባል ተብሎ የሚጠበቅ ዝናብ ከሶስት ወረዳዎች በስተቀር ሳይዘንብ በመቅረቱ በዞኑ ድርቅ እንዲከሰት እንዳደረገውና በአካባቢውም የምግብ ፣ የውሃ እና የእንስሳት መኖ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!