Fana: At a Speed of Life!

የኅብረተሰቡ ቸልተኝነት የኮቪድ-19ን ስርጭት አሳሳቢ አድርጎታል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኅብረተሰቡ የኮቪድ-19 መከላከያዎችን ያለመተግበርና ክትባት ለመውሰድ የሚያሳየው ዳተኝነት የቫይረሱን ስርጭት አሳሳቢ አድርጎታል ሲል የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱዩት አስታወቀ።
 
ኢንስቲትዩቱ ከጥቅምት 1 እስከ 7 ቀን 2014 የነበረውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
 
የኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሚኪያስ ተፈሪ፥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ቀውስ ለመግታት ኅብረተሰቡ ወረርሽኙን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን እንዲተገብር ማሳሰባቸወን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።
 
የማዕከሉ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሚኪያስ እንዳብራሩት በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየውን ቸልተኝነት ተከትሎ በሳምንቱ በኮቪድ-19 የተያዙ፣ ወደ ጽኑ ሕክምና ክፍል የገቡና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡
 
በአገር አቀፍ ደረጃ ከጥቅምት 1 እስከ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ባለው የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ 227 ሰዎች በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
 
ወረርሽኙ በአዲስ አበባ የ98፣ በኦሮሚያ የ70፣ በደቡብ የ10፣ በድሬዳዋ የ10፣ በአማራ የሰምንት ፣ በሲዳማ የስምንት፣ በሶማሌ የ20፣ በሐረሪ የሁለት እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ የአንድ ሰው ሕይወት ቀጥፏል።
 
በመላ አገሪቷ በሳምንቱ ምርመራ ከተደረገላቸው 52 ሺህ 424 ሰዎች መካከል 4 ሺህ 771 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
 
በበሽታው የመያዝ ምጣኔውም በአገር አቀፍ ደረጃ ዘጠኝ በመቶ መድረሱን ነው ዶክተር ሚኪያስ የገለጹት፡፡
 
በቫይረሱ የተያዙ 1 ሺህ 202 ሰዎች በሕክምና ማዕከላት እንደሚገኙና ከእነዚህ መካከል 600 ያህሉ የጽኑ ሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም አክለዋል።
 
በኢትዮጵያ ዴልታ የተሰኘው የኮቪድ-19 ዝርያ ከተከሰተ ወዲህ በተለይ ወደ ጽኑ ሕክምና ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱ ተመላክቷል፡፡
 
በአሁኑ ወቅት 23 ሺህ 287 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው፤ በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥርም 6 ሺህ 258 መድረሱን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
 
በአጠቃላይ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 359 ሺህ 881 የደረሰ ሲሆን 330 ሺህ 334 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.