በነገሌ ቦረና 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በነገሌ ቦረና መቆጣጠርያ ጣቢያ ሸዋ በር ኬላ በተደረገ ፍተሻ 2 ሚሊየን 659 ሺህ ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን የቦረና ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ከተያዙት ዕቃዎች ውስጥም ግምታዊ ዋጋቸው 114 ሺህ 960 ብር የሆኑ አልባሳት፣ ህገ ወጥ መድሓኒት፣ የጸጉር ማሽን እና ጫማዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም ግምታዊ ዋጋው 300 ሺህ ብር የሆነ 60 ኪሎ ግራም ሀሺሽ በቡሌ ሆራ ከተማ እና በአካባቢ ወረዳ ፖሊስ በተደረገ ክትትል ከእነተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም ከሊበን ወረዳ ፖሊስ ጋር በተሠራ ስራ ግምታዊ ዋጋው 110 ሺህ 40 ብር የሆነ 200 ኪሎ ግራም ልባሽ ጨርቅ እና ቅመማ ቅመም መያዙ ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በያቤሎ መቆጣጠርያ ጣቢያ በተደረገ ፍተሻ ግምታዊ ዋጋቸው 2 ሚሊየን 134 ሺህ ብር የሆኑ 254 ስማርት የሞባይል ስልኮች በአይሱዙ ጭነት ተሽከርካሪ ደብቆ ለማለፍ ሲሞክር መያዙን ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡
ህገ-ወጥ ዕቃዎቹ የፌዴራል ፖሊስ ከሊበን ወረዳና ቡሌሆራ ከተማ ፖሊሶች ጋር በሰራው የተቀናጀ ስራ መያዛቸውን የገለጸዉ መምሪያው÷ ይህ የተጠናከረ ስራም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡
በጥላሁን ይላማ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!