Fana: At a Speed of Life!

ከፊታችን ዓርብ ጀምሮ የፖሊዮ ክትባት በሀረርና በድሬዳዋ ይሰጣል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ የ2014 (ኤፍ ቢሲ) የመጀመሪያውን ዙር የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዕድሜያቸው ከ 5 ዓመት በታች ለሆኑ 120 ሺህ ለሚጠጉ ህፃናት ለመስጠት ዝግጅታችንን አጠናቅቀናል ሲሉ የሀረሪ ክልልና የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች አስታወቁ፡፡
ህፃናትን ለዘላቂ የአካል ጉዳትና ለሞት የሚዳርገውን የፖሊዮ በሽታ ለመከላከል÷ የቤት ለቤት የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከጥቅምት 12 እስከ 15 ድረስ እንደሚሰጥ የየቢሮዎቹ የስራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
ፖሊዮ (የልጅነት ልምሻ) በሽታ የህፃናትን የእጅና የእግር ጡንቻ የሚያዳክምና የሚያልፈሰፍስ ገዳይ በሽታ ቢሆንም÷ በሽታውን በክትባት መከላከል ስለሚቻል ዘመቻውን ለመስጠት አስፈልጓል ሲሉ የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብሳ ኢብራሂምና የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ ተናረዋል፡፡
በሀረሪ ክልል በሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ከ54 ሺህ በላይ እድሜያቸው ከ5 ዓመታ በታች የሆኑ ህፃናት ክትባቱን እንደሚያገኙ የጠቆሙት አቶ ኢብሳ÷ ክትባቱን 120 የጤና ኤክስቴንሽንና ሌሎች ባለሙዎች አማካኝነት ይሰጣል ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ዩሱፍ በበኩላቸው÷ ዘመቻው ያስፈለገው በድሬዳዋ አጎራባች አካባቢዎች የፖሊዮ በሽታ ምልክት በመታየቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዘመቻውም ከ65 ሺህ በላይ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆናቸው ህፃናት እንደሚከተቡ አስታውቀዋል፡፡
የፖሊዮ በሽታን በክትባት መከላከል ስለሚቻል ወላጆችና አሳዳጊዎች ዕድሜያቸው ከ 5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ከዚህ ቀደም የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባትን ቢከተቡም ባይከተቡም ቤት ለቤት በሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ህፃናቱን እንዲያስከትቧቸው ኃላፊዎቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በተሾመ ኃይሉ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.