ኢትዮጵያ ራሷን ከተረጂነት የምታላቅቅበት ብቸኛ መንገድ የምግብ ሉዓላዊነት ነው-የኢኮኖሚ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ከተረጂነትና ከተመጽዋችነት ለማላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተዋናዮች ተናገሩ።
የዘርፉ ተዋናዮች የአገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህል መዳበር እንዳለበትም መክረዋል።
የምግብ ሉዓላዊነት የራስን ምግብ በራስ አቅም ማምረትና የምግብ ዋስናን ማረጋገጥ መቻል ማለት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ይህን ለማድረግ የሚያስችል 74 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት እንዳላት ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ በኢትዮጵያ ከ1990 እስከ 2000 ዓ.ም ይታረስ የነበረው መሬት 9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር የነበረ ሲሆን፤ይህ አሃዝ ከ2000 እስከ 2012 ዓ.ም ወደ 12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር አድጓል።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ከ36 በመቶ በላይ አነስተኛ እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮች ከ0 ነጥብ 5 ሄክታር በታች መሬት ነው እያረሱ ያሉት።
ከ60 በመቶ በላይ አነስተኛ እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮች ከአንድ ሄክታር መሬት በታች የሚያርሱ ሲሆን፤ ከ10 ሄክታር መሬት በላይ ያላቸው በቁጥር 14 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች ብቻ ናቸው።
ዶክተር ወረታው በዛብህ የስራ ፈጠራ አሰልጣኝ፣ ዶክተር አዲስ ከበደ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፥ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ አስፋው አበበ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ሌሎች ያልተሰጣቸውን ጸጋ ይዛ በድህነት ውስጥ መሆኗ እና ዜጎቿ ለችግር መጋለጣቸው ከምንም በላይ ሊያስቆጨን ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አገራት ለስደት እየተዳረጉና እየተሰቃዩ ያሉትም አገሪቷ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን ተጠቅማ ራሷን ማሳደግ ባለመቻሏ እንደሆነ ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ሀብት ይዛ እንዴት ወጣት ልጆቿ ስራ አጥ ሊሆኑ ቻሉ?” የሚለውን ጥያቄ ሁሉም ራሱን ሊጠይቅ የሚገባው ጉዳይ ነው ሲሉም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉም የተሰጣት ፤ ነገር ግንነ ሀብቶቿን ለመጠቀም የተሳናት አገር ናት፤ የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ይህን ጸጋ ወደ ዕድል በመቀየር ከተመጽዋችነት ነፃ ልትሆን እንደምትቸል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ያላትን የእርሻ መሬት አሟጣ በመጠቀም፣ የመስኖ ልማት በማጠናከር፤ የግብርና ምርታማነቷን ማሳደግ
ኢትዮጵያ ራሷን ከተረጂነት ለማላቀቅ ብቸኛው መንገድ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ መሆኑንና በዚህም ላይ አበክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የዜጎችን የምግብ ፍላጎት በራስ የምርት አቅም የመሙላት ስራ በመከወን ከውጭ አገራት ምርት ጠባቂነት መላቀቅ ይገባልም ብለዋል።
ያደጉ አገራት በኢትዮጵያ ትከሻ ላይ መዳፋቸውን በመጫን ማደግ የለብሽም እያሏት ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ኢትዮጵያ መመንጠቅ አለባት፤ ለዚህም ጸጋዋን በአግባቡ መጠቀም ይገባታል ሲሉም ተናግረዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!