ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአየር ንብረት ለውጥ – የ100 ሚሊየን አፍሪካዊያን ስጋት መሆኑ ተጠቆመ

By Alemayehu Geremew

October 20, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ የ2014 (ኤፍ ቢሲ) እየተባባሰ በመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ 100 ሚሊየን በድህነት አረንቋ ውስጥ የሚገኙ አፍሪካውያን አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት አስጠነቀቀ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ባወጣው ሪፖርት÷ በ ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የአህጉሪቷ የበረዶ ግግሮች ሊቀልጡ ይችላሉ ተብሏል፡፡

የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርቱ ÷ የአህጉሪቷ የሙቀት መጠን በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን አፍሪካውያን ለዓየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ይሆናሉ ሲል አሳስቧል፡፡

ጆሴፋ ሊኦኔል ኮሪሳ ሳኮ የተባለች የአፍሪካ ኅብረት የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽነር ደግሞ ÷ አፍሪካ እስከ ፈረንጆቹ 2030 አፋጣኝ የአካባቢ ጥበቃ እርምጃዎች የማትወስድ ከሆነ 118 ሚሊየን በድህነት አረንቋ ውስጥ የሚማቅቁ ነዋሪዎቿ ለድርቅ፣ ለጎርፍ መጥለቅለቅ እንዲሁም ለከፍተኛ ሙቀት ይጋለጣሉ ብላለች፡፡

ኮሚሽነሯ አክላ÷ በፈረንጆቹ 2050 በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምክንያት ከሠሃራ በታች ባሉ ሀገራት ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታቸው እስከ 3 በመቶ ሊቀንስ ይችላል ብላለች፡፡

የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት በሪፖርቱ ÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ4 በመቶ ለሚያንስ የጎጂ ጋዝ ልቀት 54 ሀገራትን ተጠያቂ አድርጓል ሲል የዘገበው አልጀዚራ ነው፡፡

በዓለማየሁ ገረመው