Fana: At a Speed of Life!

ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ አካዳሚ ሊከፍት ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው የትምህርት ዘመን በአትሌቲክስ ስፖርት ብቁና የሰለጠኑ ባለሙያዎች ለማፍራት የስፖርት ሳይንስ አካዳሚ ለመክፈት መዘጋጀቱን አስታወቀ።

የስፖርት አካዳሚው መከፈት ሀገሪቱ በአትሌቲክስ ስፖርት በአለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ተመልክቷል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አበጀ ታፈረ ለኢዜአ እንደተናገሩት÷ ተቋሙ የሚገኝበት የሰሜን ተራሮች አካባቢ ለአትሌቲክስ ስፖርት ስልጠና የሚያግዝ መልካዓ ምድራዊ አቀማመጥና ተስማሚ የአየር ንብረት ያለው በመሆኑ ለዘርፉ ተመራጭ ነው።

በዘርፉ እውቀት የተካኑ አሰልጣኞችን በብዛትም ሆነ በጥራት በማፍራት የሀገሪቱን የአትሌቲክስ ስፖርት ለማሳደግ እንዲቻል ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃግብር ለማሰልጠን መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም ስርዓተ ትምህርት ቀረፃ፣ የመምህራን ቅጥርና የግብዓት ማሟላት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተውን የእሳት አደጋ በሰለጠኑ ባለሙያዎች መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል ዘንድሮ የእሳት አደጋ ማሰልጠኛ ማዕከል ለማቋቋም ዩኒቨርሲቲው እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የስፖርት አካዳሚው መከፈት ሀገሪቱን ወክለው በአለም አቀፍ መድረኮች ለሚሳተፉ የአትሌቲክስ ስፖርተኞች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያግዛል ያሉት ደግሞ የደባርቅ ከተማ የስፖርት ማህበራት ማደራጃ ስልጠናና ውድድር ቡድን መሪ አቶ አየልኝ ካሳ ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወክለው የሚወዳደሩ 85 የአትሌቲክስ ስፖርተኞች በደባርቅና አካባቢው ልምምድ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው ÷ አካዳሚው ዘርፉን ለማጠናከር እገዛው የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ አዲስ የሚከፍታቸውን ጨምሮ 25 የትምህርት ፕሮግራሞች ያሉት ሲሆን ÷ በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ ዲግሪ በመደበኛና በኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.