የሀገር ውስጥ ዜና

የሕዝቡ አንድነት ኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠር ለሚፈልጉ አካላት ስጋት ፈጥሯል – ኡስታዝ ጀማል በሽር

By Meseret Awoke

October 22, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ሕዝብ ለሀገሩ ጥቅም በአንድ ድምፅ ከመንግሥት ጎን መቆሙ ኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠር በሚፈልጉ አካላት ላይ ስጋት መፍጠሩን ኡስታዝ ጀማል በሽር አስታወቁ፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታንም ሆነ የሰሜኑን ጦርነት አስታከው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚሹ አካላት ባልጠበቁት መልኩ ኢትዮጵያውያን ከመንግሥት ጎን በመቆማቸው ያሰቡትን እንዳይፈፅሙ አድርጓል ሲሉ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ የሚታወቁት ኡስታዝ ጀማል ለኢፕድ ተናግረዋል፡፡

በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ ለሀገራቸው ዘብ መቆማቸው በራሱ ማንኛውም ማዕቀብ ቢጣል እንኳን መቋቋም የሚያስችል ነውም ብለዋል፡፡

ከግብፅ ጋር የፖለቲካና የጥቅም ትስስር ያላቸው ሀገራት የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ አቅም የሚገነባውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማስቆም ከመቼውም ጊዜ በላይ በጠላትነት መሰለፋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በየትኛውም የዓለም ሀገር ላይ ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመውሰድ ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን ቢያደርጉም አንድም ጊዜ አቋም መያዝ አለመቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያን የሚደግፉ ወዳጅ ሀገራት ከሚያደርጉት ብርቱ ትግል ባለፈ መላው ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ በመቆማቸው ነው ብለዋ፡፡

በተለይም በተለያዩ ሃገራት በስደት የሚኖረው ዳያስፖራ ብሔርና ቋንቋ ሳይለየው ለሀገሩ ቀን ከሌሊት ዘብ የቆመበት ጊዜ መሆኑን ጠቁመው÷ የኢትዮጵያን ልማት የሚጠሉ አካላት ማዕቀብ ለማስጣል የሚያደርጉትን ሴራ በማጋለጥና በመመከት ረገድ ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ጠንካራ ህብረት የተመድን እጅ በመጠምዘዝ አቋም ለማስያዝ የሚደረገውን ጥረት አስቀድሞ ለማፍረስ እገዛ እያደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!