የአፍሪካን ሴቶች ማብቃትና በጾታ እኩልነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካን ሴቶች ማብቃትና በጾታ እኩልነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ።
የምክክር መድረኩ የአህጉሪቱን ሴቶች አቅም በማሳደግ የጾታ እኩልነትን ማረጋገጥ አላማው ያደረገ ነው።
በመድረኩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ፥ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልበርግ እና የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ተገኝተዋል።
በወቅቱ የሴቶችን አቅም ለማሳደግና የጾታ እኩልነትን ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር በአፍሪካ ድህነት አሁንም የሴቶች ፈተና መሆኑን ገልጸዋል።
ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ሴቶች ቁጥር ከወንዶች በላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በንግግራቸው የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የገንዘብ አቅም ማጠናከር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህ ባለፈም የመንግስታቱን ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦች ማሳካት በሚያስችል መልኩ የጾታ እኩልነትን ማረጋገጥና የሴቶችን አቅም ማጎልበት ይገባልም ነው ያሉት።
ሰላማዊና ሁሉን አካታች የሆነ ማህበረሰብ መገንባት ግዴታ መሆኑንም አስረድተዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision