Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ ጎጃም ዞን ተፈናቃይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ የህወሃት የሽብር ቡድን ጦርነት በከፈተባቸው አካባቢዎች ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ 390 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ስለሺ ተመስገን ለኢዜአ እንደገለጹት ÷አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ካደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት በተጨማሪ የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ህጻናትን ከትምህርት ገበታቸው እንዲነጠሉ አድርጓል።

“በዚህም ወገን ለወገን ደራሽነቱን ለማሳየት እና ክፉ ቀንን ተባብሮና ተደጋግፎ ለማለፍ ተማሪዎችን ከበጎ ፈቃደኛ ግልሰቦች ጋር በማገናኘት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ ይገኛል” ብለዋል።

ተማሪዎቹ በጎንቻ፣ አነደድ፣ ሁለት እጁ እነሴ፣ ሞጣ፣ ማቻከል እና ሌሎችም ወረዳዎች በሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ አስረድተዋል።

ለመማር ማስተማር አጋዥ የሆኑ የትምህርት ቁሳቁሶችና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ተሟልቶላቸው ትምህርትቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ መሆኑንን ጠቁመዋል።

ተጨማሪ ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር የሚፈልጉ በጎ ፈቃደኞች ተመዝግበው ተማሪዎችን እየተጠባበቁ እንደሆነም ሃላፊው ገልፀዋል።
ተማሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ ከስነ-ልቦና ግንባታ ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ እና እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን ተገልጿል።

ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉትና አሁን ላይ የትምህርት ዕድል ያገኙት ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት፥ አሸባሪ ቡድኑ ትምህርታቸውን አቋርጠው እንዲሰደዱና ተስፋ እንዲቆርጡ ቢያደርጋቸውም፥ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አለሁ የሚል ወገን በማግኘታችን ተስፋችንን ለምልሟል ብለዋል።

ዞኑ ህወሓት በከፈተው ጦርነት በአካባቢያቸው መማር ያልቻሉ ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር እቅድ ይዞ እየተሰራ እንደሆነም ተመላክቷል።

የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት ከሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉና ለችግር የተጋለጡ ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጁ መሆኑንና ውሳኔ ማስተላለፉን በሚመለከት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቀደም ብሎ መዘገቡ ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.