Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በአራት ዞኖች የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ተከሰተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የልጅነት ልምሻ በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ምዕራብ ጎጃምና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች መከሰቱ በጤና ጥበቃ በኩል ተረጋግጧል ሲሉ የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ አስታወቁ፡፡
የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከሰትን ተከትሎ የክትባት ዘመቻ ከጥቅምት 12-15 2014 ዓ.ም ለተከታታይ አራት ቀናት ወረርሺኙ በተገኘባቸው ወረዳዎች እንደሚሰጥም ነው አቶ በላይ የገለጹት፡፡
የመጀመሪያ ዙር ክትባቱ የሚሰጠውም ሰላም በሆኑ አካባቢዎች ብቻ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ÷ በአሸባሪው የህውሓት ቡድን ወረራ ምክንያት ያልተረጋጉ አካባቢዎች አሁን ላይ ክትባቱ እንደማይሰጥ አረጋግጠዋል፡፡
ለዚህም ሁለተኛ ዙር ክትባት መዘጋጀቱንና የተፈናቀሉ እና በጊዜያዊ መጠለያ ያሉ ህጻናት የክትባቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አቶ በላይ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ጤና ቢሮ የክትባት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ወርቅነህ ማሞ በበኩላቸው÷ በፖሊዮ በሽታ የተጠቁ ህጻናት የሚደርስባቸው የአካል ጉዳት አደገኛና ሊቀለበስ የማይችል በመሆኑ÷ ንጽህናን በመጠበቅ ብቻ በሽታውን መከላከል ስለማይቻል በተጠቀሱት ቦታዎች የሚገኙ ህፃናት ክትባቱን በአፋጣኝ እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡
የክትባት ስራው በዋናነት ቤት ለቤት እንደሚሰጥ ጠቁመው÷ በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች፣ በእምነት ተቋማትና በጊዜያዊ ማቆያ ላሉ ህፃናት ከነገ ጀምሮ እንደሚሰጥ አቶ ወርቅነህ ማሞ መናገራቸውን ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.