የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የባይሎጂካል ጥናት ማዕከል መገንባት የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ ሞላ በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን አምባሳደር ኢቪግኒ ተርኪንን በቢሯቸው ተቀብለው አወያይተዋል።
በውይይታቸውም ሀገራቱ በሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሏቸውን ትብብሮች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው መክረዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ ሞላ ኢትዮጵያና ሩሲያ ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
በቀጣይም ከዚህ በፊት በጋራ ስንሰራባቸው ከነበሩት የትብብር ዘርፎች በተጨማሪ ሌሎች የትብብር ዘርፎችንም አካተን እንሰራለን ነው ያሉት፡፡
ነባር ትብብሮችን በማጠናከር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ÷ ሁለቱ ሀገራት ከቆየው ታሪካዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ባሻገር በሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመሯቸውን ትብብሮች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡
አምባሳደር ኢቪግኒ ተርኪን በበኩላቸው ÷ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በቴክኖሎጂው ዘርፍ በርካታ ፕሮጄክቶችን ነድፋ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ ባይሎጂካል ኤክስፒዲሽንና በምርምር መስክ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸው አንስተዋል፡፡
በስነ-ህይወት ጥናት፣ በዓሳ እና እንስሳት እርባታ እንዲሁም በአፈር ለምነት ዙሪያም እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም በስፔስ ሳይንስ፣ በኒውክሌር ሳይንስ መስኮች እና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
በቀጣይም የዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ረገድም በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለ የጠቆሙት አምባሳደሩ ÷ የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የባይሎጂካል የጥናት ማዕከል መገንባት የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ የሩሲያ ፌደሬሽን ሕዝብና መንግስት በአስቸጋሪ ጊዜ ሁሉ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እያደርጉት ለሚገኙት ድጋፍ እና ትብብር አድናቆት እና ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የሩሲያ ሕዝብ እና መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ድጋፍ እና ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ም ጠይቀዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!