Fana: At a Speed of Life!

ከጀርመን የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት በኮምቦልቻ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ከጀርመን የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት 500ሺህ ብር የሚያወጣ የምግብና አልባሳት ቁሳቁስ ከሰሜን ወሎ ተፈናቅለው በኮምቦልቻ ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

በጀርመን ሀገር ነዋሪ የሆኑትና የህብረቱን መልዕክት ይዘው የመጡት አቶ ዘውዱ ገብረ ማሪያም እንደገለፁት÷ ከሰሜን ወሎ ዞን በአሸባሪው ቡድን የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍና የድርሻችንን ለመወጣት በኮምቦልቻ ከተማ ተገኝተን ግማሽ ሚሊየን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገናል ብለዋል፡፡

ድጋፉ የተፈናቃዮችን ጊዜያዊ ችግር ሊቀርፍ የሚችልና የዕለት ደራሽ ምግቦች ሲሆኑ÷ 50 ኩንታል ነጭ ዱቄት ፣ 10 ኩንታል ክክ ፣ 150 ጋቢ፣ 500 ሊትር ዘይትና ሌሎች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ፓስተር መኮንን ድሪባ በበኩላቸው÷ እኛ ኢትዮጲያውያን በየጊዜው በሚገጥመን ፈተና ብንፈተንም በአሸናፊነት እየተወጣነው እዚህ ደርሰናል ብለዋል፡፡

ይህ ወቅት ጊዜያዊ ችግር በመሆኑ ሁሉም ህዝብ በአንድነት በመቆምና የተቸገሩ ወገኖች እንዳይከፋቸው አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ችግሩ መጠነ-ሰፊ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን እንዲወጣም ነው ያሳሰቡት ፡፡

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናት ወጣቶች ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዘሪቱ ሁሴን ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት÷ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ያደረው ድጋፍ ለወገኖቻችን እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በተመሳሳይ ድጋፍ እንዲደርጉ ጠይቀው ÷ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በዘሩ ከፈለኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.