Fana: At a Speed of Life!

በህወሓት መቃብር ላይ ለትውልድ የሚተላለፍ የድል ታሪክ እንጽፋለን ያሉ የወሎ ወጣቶች እየዘመቱ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተለያዩ የወሎ አካባቢዎች ደሴ ከተማ የተሰባሰቡ ወጣቶች የሽብርተኛውን እና ወራሪውን ትህነግ ግብዓተ መሬት በመፈፀም ዘመን ተሻሪ የድል ታሪክ እንጽፋለን በማለት ወደ ግንባር እየዘመቱ ይገኛሉ።
 
የአማራ ክልል መንግሥት ያስተላለፈውን “ሁሉም ወደ ወሎ ይትመም፣ ይዝመት” የክተት ጥሪ ተቀብለው የደሴና የአካባቢው ወጣቶች ወደ ግንባር በመዝመት ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከአማራ ልዩ ኀይል ጎን በመሰለፍ ላይ ናቸው።
 
ከኮምቦልቻ ከተማ ተነስቶ ወደ ሐይቅ እየዘመቱ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ወጣት አማረ ፈቃደ በኮምቦልቻ ከተማ ወጣቶች እየተደራጁ በመዝመት ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል።
 
እኔም የጠላት የሐሰት የፕሮፖጋንዳ ጋጋታ ሳይበግረኝ ቀድሜ ወደ ሐይቅ እየዘመትኩ ነው ፤ወደ ግንባር ሄደን መከላከያ እና ልዩ ኀይላችንን በመቀላቀል አሸባሪውን ትህነግ እንፋለመዋለን ብሏል።
 
ወጣቱ አሸባሪውን ትህነግ ለመቅበር ወጣቶች እየተደራጁ ወደ ግንባር መዝመት እንዳለባቸውም ነው ያሳሰበው፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት መምበር ፍቃዱ “ወራሪውን ተደራጅቶ መመከት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፤በመዝመት አሸባሪውን ትህነግ ከምድረ ገጽ ማጥፋት የወጣቶች ብቸኛ አማራጫችን መሆኑን ገልጿል፡፡
 
በተለያየ መንገድ ወጣቱን የሚያዘናጉ አካላት ከድርጊታቸው ታቅበው ወጣቱ ለህልውናው እንዲታገል ማነሳሳት እንደሚገባም አስተያየቱን ሰጥቷል።
 
ወጣት መሐመድኑር ከድር “ሀገር የሁሉም ናትና ወጣቶች ሀገራችንን ማስከበር አለብን፤ በክልላችን መንግሥት የተላለፈውን የክተት ዘመቻ ጥሪ ተቀብለን አሸባሪውን ባለበት ለመፋለም ቆርጠን ተነስተናል” ብሏል።
 
ትግሉ የአሸባሪውን ትህነግ ግብዓት መሬት እስከመፈፀም ነው፤ ስለዚህ ወራሪው እያለ አንድም ቀን ደሴ መቀመጥ አያስፈልግም፤ ከጠላት ጋር እዛው ግንባር መዋደቅ እና መደምሰስ ይገባል፤ሁላችንም በጋራ ጠላትን ባለበት ልንፋለም ተነስተናል ነው ያለው፡፡
 
ሌላኛው ዘማች ወጣት ደሳለኝ ሲሳይ በበኩሉ መከፋፈሉ ያጠፋናል፤ ሁሉም ወጣት ሽብርተኛው ትህነግን መቅበሪያው ጊዜው አሁን ነውና ራሳቸው እና አካባቢያቸውን ለመጠበቅ በቁርጠኝነት መነሳታቸውን ይናገራል፡፡
 
ወጣት ደሳለኝ ወጣቶች በአንድነት ቆመን ጠላትን በመደምሰስ ደማቅ ታሪክ እንጽፋለን ማለቱንም አሚኮ ዘግቧል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.