Fana: At a Speed of Life!

ኅብረተሰቡ በአሸባሪው ህወሓት የሐሰት ውዥንብር ሳይደናገጥ አካባቢውን ጸንቶ እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት13፣2014 (ኤፍ ቢሲ)ኅብረተሰቡ በአሸባሪው ህወሓት ሐሰተኛ ውዥንብር ሳይደናገጥ አካባቢውን በፅናት እንዲጠብቅ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር አባላት ጥሪ አቀረቡ።
ሕዝቡ አሸባሪውን የህወሓት ወራሪ ኃይል በመመከት ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው ሠራዊት እያሳየ ያለውን ደጀንነት ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል።
 
የአመራር አባላቱ አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል በሐሰት ፕሮፖጋንዳ ኮምቦልቻ፣ ደሴና አካባቢዋን ተቆጣጥሬያለሁ የሚለው ከቡድኑ ተፈጥሯዊ ባህሪይ የመነጨ ‘ነጭ ውሸት’ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።
 
አሸባሪው ኃይል በሐሰት ፕሮፓጋንዳው ይዣቸዋለሁ ያላቸው የደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ሠላማዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ መሆናቸውን መመልከታቸውን ገልፀዋል።
 
ለሽብርተኛው ቡድን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሰላባ ባለመሆን የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሌሎች የጸጥታ አካላትን ተጋድሎ በደጀንነት መደገፍ እንደሚገባም አመልክተዋል።
 
የአብን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዩሱፍ ኢብራሂም÷ ወራሪው የሽብር ቡድን ሐይቅ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ እና በአካባቢው ያሉ ከተሞችን ተቆጣጥሪያለሁ ብሎ ማስወራቱ ድርጅቱ በውሸት ተወልዶ በውሸት ሞት አፋፍ ላይ ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
 
ማኀበረሰቡም የድርጅቱን ጸረ ሕዝብነትና ሐሰተኝነት በመገንዘብ በየአካባቢው ሆኖ መመከትና ለሠራዊቱ እያደረገ ያለውን ደጀንነት ማስቀጠል ይገባዋል ነው ያሉት።
 
ወጣቱ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ንብረት ለመዝረፍና ሕዝቡን ለማጎሳቆል የወረራ ተግባሩን የቀጠለውን የሽብር ቡድኑን ኃይል በጽናት እንዲመክትም ጥሪ አቅርበዋል።
 
የአብን የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጋሻው መርሻ በበኩላቸው÷ በጦርነት ቀጠና ያለውን ማኅበረሰብ በጥፋት ተግባር ላይ የተሰማራውን የሽብርተኛውን ኃይል በመተባበር ማጥፋት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ለሠራዊቱ ደጀን ከመሆን ባሻገር አደረጃጀት ፈጥሮ ጸጉረ ልውጦችን የመቆጣጠር ስራ በማከናወን የህልውና ተጋድሎው ግቡን እንዲመታ በጽናት መታገል እንደሚገባም አመልክተዋል።
 
ያለ የሌለ ኃይሉን አሰባስቦ በሕዝብ ላይ መጎሳቆል እያስከተለ ያለውን ወራሪውን ሽብርተኛ ኃይል ለመቅበር በሚደረገው ተጋድሎ ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.