ማህበረሰቡ ለመከላከያ ሰራዊት እያሳየ ያለውን ደጀንነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ማህበረሰቡ ለመከላከያ ሰራዊትና ለጸጥታ አካላት እያሳየ ያለውን ደጀንነት አጠናክሮ እንዲቀጥል የደሴ ከተማ አስተዳደር ጥሪ አቀረበ።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ አበበ ገ/መስቀል በህወሓት የሽብር ቡድን የተከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ መላ ኢትዮጽያዊያን በጋራ መሰለፋቸውን ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰቡም በጦር ግንባር እየተዋደቀ ላለው የጸጥታ ኃይል ደጀንነቱን እያሳየ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ነዋሪዎቹ የሎጅስቲክ ድጋፍ በማድረግ፣ ቁስለኛ በማንሳት እና ትጥቅ በማቅረብ እያሳዩት ያለው ደጀንነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም በበኩላቸው÷ማህበረሰቡ አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ለጁንታው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሳይንበረከክ አካባቢውን እየጠበቀ ሰራዊቱን የሚያግዘው ህዝብ ለሀገሩ ለሰራው ውለታ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል ሲሉም ገልጸዋል።
ይህንን የህልውና ዘመቻ ለመቀላቀል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተመመ ላለው ኢትዮጵያዊም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሙሉቀን አበበ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!