Fana: At a Speed of Life!

ለተፈናቀሉ ወገኖች ከምእራብ ጎንደር ዞን ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የአይነት ድጋፍ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት አልባሳት መሰብሰቡን የምዕራብ ጎንደር ዞን የሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ኃይል በግፍ ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወገኖች መላው ኅብረተሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በምዕራብ ጎንደር ዞንም በግፍ ተፈናቅለው በደባርቅ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች አንድ ቤተሰብ ለአንድ ቤተሰብ በሚል መሪ መልዕክት ፤ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት በአይነትና በመጠን የአልባሳት ድጋፍ መሰብሰቡን የዞኑ ሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት የሽዋስ ገልጸዋል።

የአልባሳት ድጋፉ በዞኑ ባሉ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰበ ሲሆን ÷ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀትና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ወይዘሮ ሰናይት ገልጸዋል።

የአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በእናቶችና ህጻናት ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና በደል ታሪክ ይቅር የማይለው ነው ያሉት ወይዘሮ ሰናይት÷ የዞኑ ኅብረተሰብ የተፈናቀሉ ወገኖችን በሚቻለው መጠን ለመደገፍ ያሳየው ቁርጠኝነትና ወገናዊ ስሜት ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በሴቶች ሊግ አስተባባሪነት “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ቤተሰብ” በሚል መሪ መልዕክት የተቋቋመው ግብረ ኀይል የሴቶችንና ወጣቶችን አደረጃጀት በማስተባበር ተፈናቃዮችን መልሶ ለማደራጀት የቤት ቁሳቁስ ከኅብረተሰቡ እየሰበሰበ መሆኑንም ኃላፊዋ ገልጸዋል።

የጥፋት ቡድኑ ግብዓተ መሬቱ እስከሚፈጸም ለተፈናቀሉ ወገኖች ሀብት የማሰባሰብ ሂደቱ ይቀጥላል ያሉት ኃላፊዋ ÷ ድጋፉን ላበረከተው የዞኑ ኅብረተሰብ “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ቤተሰብ” የድጋፍ ሀብት ሰብሳቢ ግብረ ኀይል እንዲሁም ለሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀት ምስጋና ማቅረባቸዉን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.