
የደቡብ ሱዳን የፓለቲካ ሀይሎች የሽግግር መንግስት ምስረታ ስምምነቱን በፍጥነት ወደ ተግባር ሊቀይሩት ይገባል- አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ሱዳን የፓለቲካ ሀይሎች የደረሱበትን የሽግግር መንግስት ምስረታን ሳያራዝሙ ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጠየቁ።
ዋና ፀሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሀመት ጋር ውይይት አድርገዋል።
ከውይይቱ በኋላም በሰጡት መግለጫ የሀገሪቱ የፓለቲካ ሀይሎች ከመቸውም ጊዜ በላይ ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተው የሚሰሩበት ወቅት ነው ብለዋል።
ዋና ፀሃፊው ምክንያት እያስቀመጡ የሽግግር መንግስት ምስረታውን ለማስረዘም የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት።
በሌላ በኩል በሊቢያ ፣ ሳሃል ቀጠና እና በቻድ ሀይቅ አካባቢ የሚፈፀሙ ሽብር ጥቃቶች እና የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአፍሪካ ህብረት ጋር የተጠናከረ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶን ከአህጉሪቱ ውጭ በሚመጡ ሰላም አስከባሪዎች ከማረጋጋት ይልቅ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪዎችን አቅም በማጠናከር በራስ አቅም ሰላምን ማስፈን
እንደሚገባ ገልፀዋል።
ዋና ፀሃፊው አፍሪካ ከሉላዊነት እና ከአለም አቀፍ ንግድ ፍትሃዊ ድርሻ እንዲኖራት የተሻለ ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ከሀምሌ ወር ጀምሮ የሚተገበረው አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ለአህጉሪቱ እድገት የራሱ ሚና እንደሚኖረውም ዋና ፀሃፊው ተናግረዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በሰጡት መግለጫ÷ የማግለል አካሄድን በማስወገድ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አለም አቀፍ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘውን የበረሃ አንበጣ በጋራ መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በስላባት ማናየ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision