በተራድኦ ተቋማት ስም የሚንቀሳቀሱ ተቋማት በሃገር ሉዓላዊነት ላይ ተጽእኖ እንዳያደርሱ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል -ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በተራድኦ ተቋማት ስም የሚንቀሳቀሱ ተቋማት በሃገር ሉአላዊነትና አንድነት ላይ ተጽእኖ እንዳያደርሱ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ሲሉ የህግና የታሪክ ምሁራን ተናገሩ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ እና ታሪክ መምህር ዶክተር አልማዉ ክፍሌ÷ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የሃገራትን የፖለቲካ ስንጥቃትን ተጠቅመው የግል ጥቅማቸውን ሲያስከብሩ እንደቆዩ ያብራራሉ ።
በመንግስታቱ ድርጅት ስር ያሉ ተራድኦ ድርጅቶችን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ የተራድኦ ተቋማት በሊቢያ፣ የመን ፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታን እና መሰል ሃገራት ላይ የመንግስታቸውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲያስፈጽሙ እንደቆዩና ለሃገራቱ ሰብአዊ ቀውስ አባባሽ ሆነዉ መቆየታቸውን ዶክተር አልማው አስረድተዋል ።
የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ያሬድ ሃይለ መስቀል በበኩላቸው÷ የምዕራባውያኑ መንግስታት ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማግለል መሰል ተቋማትን እንደሚጠቀሙባቸው ገልጸዋል።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ ዘመድኩን መካሻም ድጋፍን የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም በማይጎዳ መንገድ እንዲሆን ማድረግ ይገባል ይላሉ።
ይህን የተቋማቱን አካሄድ በመረዳትም መንግስት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል የማድረጉን ስራ ማስቀጠል እንደሚገባውም ምሁራኑ ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡
በዘላቂነት ሃገራዊ አቅምን መጠቀም፣ ጠንካራ የስራ ባህል እንዲዳብር መስራት እና የፖለቲካውን ስንጥቃት በማረቅ የመሰል ተቋማት ተጽእኖን መግታት እንደሚገባም ተናግረዋል ።
በአወል አበራ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!