የምግብና መጠጥ ማሸጊያዎች ዲዛይን በፕላስቲክ መልሶ ዑደት ሥራ ላይ ተፅእኖ አሳድሯል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምግብ እና መጠጥ ማሸጊያዎች ላይ የሚጨመሩ ቀለማት፣ የጠርሙሶች ዲዛይን እና የምርት መግለጫ ደረጃዎች የፕላስቲክን መልሶ ዑደት (ሪሳይክሊንግ) ስራ ከባድና ዋጋ የሚያሳጣ አድርጎታል መባሉን ጥናቶች አመላከቱ፡፡
ይህ የተገለፀው÷ ፔትኮ ኢትዮጵያ የተሰኘ ሀገር በቀል የልማት ድርጅት ከፌደራል አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ባዘጋጅው ዓመታዊ ጉባዔ ነው፡፡
በጉባዔው የቀረቡ ጥናቶች እንዳመላከቱተም÷ ፕላስቲክን መልሦ መጠቀም (ሪሳይክል የማድረግ) ሥራ በአሁኑ ወቅት በግሉ ዘርፍና በመንግስት አካላት በሰፊው እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩ ብሎም በሚልየን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ይሁን እንጂ የመጠጥ ምግብና መድሃኒት አምራቾች የሚጠቀሟቸው ቀለማት፣ ያላቸው የፕላስቲክ ማሸጊያዎች፣ ክብደታቸው እንዲሁም ዲዛይናቸው ምቹ ያለመሆኑ በዘርፉ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል የውኃ፣ የለስላሳ እና የምግብ አምራቾች ቁጥር እየተስፋፋ ቢሆንም÷ በሀገሪቱ ያሉ ፕላስቲክን መልሶ ስራ ላይ የሚያውሉ ድርጅቶች አለመበራከታቸው እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ መገኘታቸው፤ የድጋፍ ማጣትና የአቅም ውስንነት ሰፊ ክፍተት መፍጠሩምን ጥናቶቹ አመላክተዋል፡፡
በጉባዔው ላይ ፕላስቲክን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ሥራ ዙሪያ ጉልህ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስክር ወረቀትና ሽልማት መሰጠቱን ከፔትኮ ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!