መንግስት የህዝቡን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ በትኩረት ይሰራል-አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ የተመሰረተው መንግስት የህዝቡን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ ም የተካሄደው 6ኛ ዙር ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጸጥታ አካላት የምስጋና እና እውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት÷ቀደም ሲል በክልሉ ይታዩ የነበሩ የጸጥታ ስጋቶች የቀነሱበት እና የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል የታየበት ነው።
በዚህም በተከናወነው ቅንጅታዊ ስራዎች እና በተመዘገበው ውጤት ህብረተሰቡ ካለ ስጋት የእለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የተካሄደው 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ እና የክልሉ መንግስት ምስረታ ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ለስኬታማነቱም ህዝቡ እና የጸጥታ አካላቱ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር አመላክተዋል።
አዲሱ የክልሉ መንግስትም መላውን ህዝብ በእኩል የሚያስተዳድር እና በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን በመግለጽ÷ በተለይ የሰላም እና የልማት ተግባራቶችን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።
የክልሉ ሰላም በማረጋገጥ ረገድ የጸጥታ አካላቱ የተቀናጀ ስራ ምስጋና ያቀረቡት የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ጥላሁን ዋደራ በበኩላቸው÷ይህ ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነር ነስሪ ዘካርያ በበኩላቸው÷ በክልሉ በተቀናጀ መንገድ እየተከናወነ የሚገኘው የጸጥታ ስራ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ነው ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!