Fana: At a Speed of Life!

በወሎ ለተፈናቀሉ እና በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ እና በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።
 
ድጋፉ የአይነት እና የገንዘብ ሲሆን፥ በሰሜን እና ደቡብ ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ጥቃት ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ነው ተብሏል።
 
የአይነት ድጋፉ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ አምስት ተሳቢ ምግብ ነክ እና የንጽህና መጠበቂያ እንዲሁም አልባሳትን ያካተተ ነው።
 
ከዚህ በተጨማሪም በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ እንስሳት መኖ የሚሆን 11 ተሳቢ መኖ እና ለአንድ ወር አገልግሎት ሰጥተው የሚመለሱ 16 የውሃ ቦቴዎች ድጋፍ ተደርጓል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት÷ ምንም እንኳን ሀገራችን በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ብትሆንም በኢትዮጵያዊ አንድነት እና አብሮነት ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትን እና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎችን በሞራል እና በተለያዩ ተግባራት ለማገዝ ከሶስት ቢሊየን ብር በላይ በመሰብሰብ ድጋፍ ስናግዝ እና ስናበረታታ ቆይተናል ብለዋል፡፡
 
በቀጣይም የሚደረገው ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
 
አሁንም በቦረና ዞን በድርቅ ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ እንዲሁም በወሎ እና አካባቢው ህውሓት በከፈተው እኩይ ጦርነት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ እና ጉዳት እንዳይደርስባቸው የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎችን እና ባለሀብቶችን በማስተባበር ድጋፉን መሰባሰቡን ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
 
ለወገኖቻችን ደራሾች እኛው ነን ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ ሌሎች አካላት በተለያዩ መንገድ እርዳታ ሊሰጡን ይችላሉ ነገር ግን እርዳታው ይዞብን የሚመጣውን ጣጣ እያየን በመሆኑ÷ ኢትዮጵያውን ከተጋገዝን እና ከተረዳዳን አቅማችንን ማሳየት እንችላለን ብለዋል፡፡
 
የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩ በበኩላቸው÷አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን የሁሉም እናት ናት፤ ልጅ ሲቸገር ደግሞ ወደ እናቱ ነውና የሚጮኸው የከተማ አስተዳደሩ እና የከተማዋ ነዋሪዎች ላደረጉት ድጋፍ በቦረና ዞን ስም አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡
 
በይስማው አደራው
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
 
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.