የማረሚያ ቤት ሠራተኞችና ታራሚዎች ለሠራዊቱ የደም ልገሳና የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የማረሚያ ቤት ሠራተኞችና ታራሚዎች በግንባር ለሚፋለመው የጸጥታ ኃይል የደም ልገሳና የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።
የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ኮማንደር ቀፀላ ደበበ እንዳሉት፤ የህግ ታራሚዎቹ የመንግስትን የድጋፍ ጥሪ በመቀበል ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ከዚህ በፊት ከስጋና ሻይ ወጪያቸው 300ሺህ ብር ቀንሰው ለመከላከያ ሠራዊቱና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
ዛሬ ደግሞ ህይወት ለመታደግ የሚያሰችል የደም ልገሳና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
ከ150 በላይ የማረሚያ ቤቱ ታራሚዎችና ሠራተኞች ደም የለገሱ ሲሆን፥ በእለቱ በተካሄደ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ 18ሺህ ብር አዋጥተው መስጠታቸው ታውቋል።
ከማረሚያ ቤቱ ሠራተኞች መካከል በሰጡት አስተያየት፥ “አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በወሎ ምድር ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር በሚደረገው ጥረት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅቺያለሁ” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ለመከላከያ ሠራዊቱና ለልዩ ሃይሉ የወር ደመወዛቸውን መለገሳቸውን ጠቅሰው፤ ዛሬም በግንባር ጉዳት የሚደርስበትን የወገን ሃይል ህይወት ለመታደግ ደም በመለገሳቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የህግ ታራሚዎች በበኩላቸው፥ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት መንግስታዊ ስልጣኑን ተጠቅሞ ብዙ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሷል።
ወጣቶችን ከሀገራቸው ከማፈናቀል ጀምሮ የተለያዩ ምድራዊ ግፎች በአሸባሪው ቡደን ሲፈጽሙ እንደነበርም አመልክቷል።
በህግ ጥላ ስር ቢሆኑም አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገውን ጥረት ለማምከን በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ደም በመለገስና በገንዘብ ድጋፍ በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።