ዓመታዊው የጤና ዘርፍ የምክክር ጉባኤ ከጥቅምት 19 ጀምሮ በጅግጅጋ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 23ኛው ዓመታው የጤና ዘርፍ የምክክር ጉባኤ ከፊታችን ጥቅምት 19 ጀምሮ ለሶስት ቀናት በጅግጅጋ ከተማ የሚካሄድ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ጉባኤው “ ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓት በአዲስ ምዕራፍ ” በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 19 እስክ 21 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ በሰጡት መግለጫ፥ በጉባኤው የጤና ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ የሁሉም ክልል የጤና ቢሮ ሃላፊዎች፣ አጋር አካላት እና የተጠሪ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ይሳተፋሉ ብለዋል።
በጉባኤው መጀመሪያው ቀን ማለትም ጥቅምት 19 በጂግጂጋና አከባቢው የመስክ ጉብኝት የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ሞዴል የሆኑ የቤተሰብ ቤት እና ሞዴል የጤና ተቋማት የሚጎበኙ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ደግሞ መደበኛ ጉባኤው ይካሄዳል ብለዋል።
በጉባኤው 400 ሰዎች የሚሳተፉ መሆኑን ጠቁመው የኪቪድ 19 ፕሮቶኮል መመሪያዎች በተጠበቀ መልኩ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጉባኤውም የ2013 ዓ.ም የጤናው ዘርፍ አፈጻጸም የሚዳሰስ መሆኑን ጠቁመው በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት የሚካሄድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በጤናው ሴክተር በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተያዙ ዋና ዋና ግቦችን በጋራ ለማሳካትም የመግባቢያ ሰነድ የሚፈረም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጉባኤው በስራ አፈጻጸማቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የጤና በላሙያዎች እውቅና የሚያገኙ መሆኑንም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከሁሉም ክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተመረጡ የጤና ባለሙያዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በወጣው መስፈርት መሰረት ተወዳድረው ለአሸናፊዎቹ እውቅና ይሰጣል ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ ለየት ያሉ ግኝቶችን የፈጠሩ ተመራማሪዎችም የሚሸለሙ መሆኑንም ዶክተር ተገኔ ጠቅሰዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!