Fana: At a Speed of Life!

በቦረና በተከሰተው ድርቅ የምግብ እጥረት እንዳያጋጥም በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው-አቶ አወሉ አብዲ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ የምግብ እጥረት እንዳያጋጥም በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡
 
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በባሌ፣ ጉጂ እና ሀርርጌ ዞኖች ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል የሚያመላክቱ ሁኔታዎች በመኖራቸው ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ጥናት መገባቱን ተናግረዋል፡፡
በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ለምግብ እጥረት እና ተያያዥ ችግሮች የተጋለጡ ተጎጂዎችን የመለየት ስራ መሰራቱን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡
 
ለችግሩ የተጋለጡ ዜጎች የምግብም ሆነ የጤና ድጋፍ እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ ለእንስሳት መኖ የማቅረብ ስራም እየተሰራ ነው ብለዋል።
 
በቦረና አጎራባች አካባቢዎችም ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል አመላካች ሁኔታዎች እንዳሉ ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት።
 
የጥናት ቡድኑ የደረሰበትን ውጤት መሰረት በማድረግም አስፈላጊ ስራዎችን ሁሉ ለመስራት ክልሉ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አቶ አወል አስረድተዋል።
 
ባለሃብቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚችሉትን እገዛ በማድረግ ችግሩን በጋራ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ከመንግስትና ከተረጂዎች ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ያጋጠመውን ተፈጥሯዊ ችግር ለፖለቲካ ፍጆታ የሚጠቀሙ አካላት እንዳሉ አንስተው÷ ከዚህ ድርጊት መቆጠብ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
 
በዙፋን ካሳሁን
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.