Fana: At a Speed of Life!

ጎማ በጣም ከጮኸ የመተንፈሱ ምልክት ነው! – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር መከላከያ ሠራዊታችን የሚመራው የወገን ጦር፣ በሕዝባችን ያልተቋረጠ ደጀንነት ሰሞኑን በኩታበር፣ ተሁለደሬ፣ ወረባቦና ጭፍራ ግንባር ወረራ በፈጸመው ጠላት ላይ ፀረ ማጥቃት ርምጃ ወስዷል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።

ወራሪውን መንጋ ለመመከት፣ ለመቀልበስና ለመቅበር ቁልፉ መፍትሔ የተደራጀ የሕዝብ ንቅናቄ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው ፥ መላው ሕዝባችን በተለይም ወጣቶች እያደረጋችሁ ያላችሁትን ተጋድሎ በማጠናከር የሕዝባችንን ህልውና፣ ክብርና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክን እንድትጽፉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል ብሏል።

ወራሪው የጁንታ ቡድን ለጋላቢዎቹ ‘‘በሁለት ሳምንት አዲስ አበባ እገባለሁ’’ ብሎ ፎክሮ እንደነበር መግለጫው አስታውሶ፥
ከንቱ ሕልሙ በጀግኖቹ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ተጋድሎ ወደ ቀን ቅዠት መቀየሩን አስረድቷል።

ጎማ በጣም ከጮኸ የመተንፈሱ ምልክት መሆኑን በመግልጽ፥ መላው የወገን ጥምር ጦርና ደጀኑ ሕዝብ ከብረት የጠነከረ ኅብረትንና ንቅናቄውን በማጠናከር፣ አሸባሪው ቡድንና መንጋው የገባበት ገብተህ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት፣ ህልውናህን አስከብር ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መልዕክቱን አስተላልፏል።

ለትግራይ ሕዝብ፤ ለእናትና አባቶች ባስተላለፈው መልዕክትም፥ ለጥቂት ቅዠታሞች ብላችሁ የነገ ተስፋችሁ የሆነውን ተተኪ ትውልድ ለከንቱ ዓላማ እንዳትማግዱ፣ ቆም ብላችሁ በማስተዋል ለሀገራችሁ ጥብቅና እንድትቆሙ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ ያቀርብላችኋል ብሏል።

መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል።

ጎማ በጣም ከጮኸ የመተንፈሱ ምልክት ነው!

በሀገር መከላከያ ሠራዊታችን የሚመራው የወገን ጦር፣ በሕዝባችን ያልተቋረጠ ደጀንነት ሰሞኑን በኩታበር፣ ተሁለደሬ፣ ወረባቦና ጭፍራ ግንባር ፀረ ማጥቃት ርምጃ ወስዷል።

በተመረጡ የጁንታው አሸባሪ ቡድን ማሠልጠኛዎች፣ የጦር ማደራጃና መገናኛ አውታሮች፣ የጸጥታ አካላት፣ አልባሳትና መሣሪያዎች ማምረቻ ላይ በንሥሩና በጀግናው የአየር ኃይላችን እንዳይነሡ ተደርገው ተመተዋል።

በየግንባሩ በገፍ የሚያሰልፈው ኃይልም ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮኛ ሆኗል። ጠላት የሚተማመንባቸው ከባድ መሣሪያዎቹ መክነውበታል።

በዚህም ምክንያት በጁንታው መንደር ጩኸትና ልቅሶ በርክቷል።

የትሕነግ ሰሞነኛው ጩኸት የመተንፈሱ ምልክት ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥትን የተኩስ አቁምና ከትግራይ ክልል ጠቅልሎ የመውጣት ውሳኔን እንደ ሽንፈት ቆጥሮት ነበር።

ለጋላቢዎቹ በሁለት ሳምንት አዲስ አበባ እገባለሁ ብሎ ፎክሮ ነበር።

ሕልሙ ግን በጀግኖቹ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ተጋድሎ ወደ ቀን ቅዠት ተቀይሯል።

በዚህም የተነሣ ጥቅምት 24 ቀን በግፍ ለጨፈጨፈው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሂሳብ አወራረድበታለሁ ላለው ሕዝብ ተማጽኖውን በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ሁኔታው የወደዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይመርጡ ሆኖበታል።

በአንድ በኩል ጦርነቱ አብቅቷል መከላከያም እጁን ይስጥ ይላል።

ይሄን ይረሳውና መፍትሔው ፖለቲካዊ በመሆኑ በሀገራዊ ምክክሩ አሳትፉን ይላል። የአሞሮች ጩኸት የሙታንን መብዛት የሚያሳይ ነው።

መላው ሕዝባችን፤ አኩሪ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ያለው መላው የጸጥታ ኃይላችን ለአፍታም ቢሆን ግራ ለተጋባው ወራሪና ባንዳ የሽብር ቡድን ቅጥፈት ጆሮ አይሰጠውም።

ለጦር ግንባር እንጂ ለወሬ ግንባር ቦታ የለውም። ሕዝቡም እየተነፈሰ ለሚጮኸው ጎማ ቁብ አልሰጠውም።

ደጀንነቱና ኅብረቱን አጠናክሮታል። አሁን የሠራዊታችን ትኩረት በአቀባበሩ ላይ ነው። ሞቱ እንደማይቀር ተረጋግጧልና።

ወራሪውን መንጋ ለመመከት፣ ለመቀልበስና ለመቅበር ቁልፉ መፍትሔ የተደራጀ የሕዝብ ንቅናቄ በመሆኑ መላው ሕዝባችን በተለይም ወጣቶች እያደረጋችሁ ያላችሁትን ተጋድሎ በማጠናከር የሕዝባችንን ህልውና፣ ክብርና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክን እንድትጽፉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

ለትግራይ ሕዝብ፤ እናትና አባቶች ለጥቂት ቅዠታሞች ብላችሁ የነገ ተስፋችሁ የሆነውን ተተኪ ትውልድ ለከንቱ ዓላማ እንዳትማግዱ፣ ቆም ብላችሁ በማስተዋል ለሀገራችሁ ጥብቅና እንድትቆሙ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ ያቀርብላችኋል።

ጎማ በጣም ከጮኸ የመተንፈሱ ምልክት ነውና መላው የወገን ጥምር ጦርና ደጀኑ ሕዝብ ከብረት የጠነከረ ኅብረትንና ንቅናቄውን በማጠናከር፣ አሸባሪው ቡድንና መንጋው የገባበት ገብተህ በመቅጣት፣ ህልውናህን አስከብር!

ውኃ የሚወስደው እሾህ ይጨብጣል። ጁንታው ያድነኛል ያለውን ሁሉ ለማድረግ መፍጨርጨሩ የሚጠበቅ እንጂ የሚያስደንቅ አይደለም።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.