የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራን በተቋሙ ማድረግ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ በተቋሙ ማድረግ መጀመሩን ገለፀ።
ኢንስቲትዩቱ 6 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ በሽታ ምልክት ታይቶባቸው በለይቶ ማቆያ ማዕከል ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ አስታውቋል።
እነዚሁ ሰዎች ለቫይረሱ ምርመራ ናሙና የተወሰደላቸው መሆኑንና የሶስቱ ናሙና ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩን ትናንት መግለፁ የሚታወስ ነው።
በዛሬው ዕለት የሶስቱ ናሙናዎች ውጤት እንደደረሰው እና ሶስቱም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸዉ መረጋገጡን ገልጿል።
በተጨማሪም እዚሁ በኢንስቲትዩቱ የተወስዱ የሶስቱ ናሙና በተቋሙ ምርመራ ተደርጎ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል ብሏል።