የሀገር ውስጥ ዜና

የብልፅግና እና የቻይናው ኮሚዩኒስት ፓርቲ ግንኙነታቸው በሚጠናከርበት ሁኔታ መከሩ

By Meseret Awoke

October 28, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ጃኦ ዚዩን የፓርቲዎቹ ቀጣይ ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡

ዶክተር ቢቂላ በውይይቱ ወቅት እንዳነሱት፥ ቻይና ለኢትዮጵያ እድገትና ብልፅግና የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ታደንቃለች፡፡

በተለይም በቅርቡ ኢትዮጵያ የገጠማትን የውስጥ ፈተና በራሷ መፍታት እንደምትችል ቻይና የያዘችውን አቋም የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ የዓለም ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት እንዲገታ ቻይና በመርህ ላይ በመቆም ላደረገችው ድጋፍም አመስግነዋል፡፡

አያይዘውም የብልፅግና ፓርቲ ከቻይና የብልፅግና ስኬቶች ብዙ ልምዶችን እንዳገኘና ወደፊትም ልምዶችን እንደሚቀስም አስታውቀዋል፡፡

የቻይና አምባሳደር ጃኦ ዚዩነ በበኩላቸው ÷ የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ምንጊዜም ለኢትዮጵያ እድገትና ብልፅግና ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም መደጋገፍን መሰረት ባደረገ መልኩ ለጋራ ዓላማና ፍላጎት እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!