Fana: At a Speed of Life!

የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፊሰሮችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፊሰሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ በመረጃ ኪነሙያ በማሰልጠን በዛሬው ዕለት አስመረቀ።

የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅ እንዲሁም የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተልዕኮውን ከመወጣት ጎን ለጎን በስሩ በሚገኘው የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በተለያዩ ጊዜያት ኦፊሰሮችን በመረጃ ኪነ ሙያ በማስመረቅ አሰማርቷል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በዘርፉ የካበተ ልምዱን ወደ ጉረቤት ሀገር በማሻገር ከደቡብ ሱዳን አቻ የመረጃና ደኀንነት ተቋም ከሆነው ናሽናል ሴኩሪቲ ሰርቪስ የመረጃ ኦፊሰሮችን በመጀመሪያ ዙር ተቀብሎ በመረጃ ኪነሙያ በማሰልጠን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በምረቃ ስነሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት÷ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፊሰሮችን በመረጃ ኪነሙያ አሰልጥኖ ማስመረቁ በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን አጋርነትና ትብብር ይበልጥ ያጠናክራል።

ሁለቱ ሀገራት ረጅም አመታት ያስቆጠረ ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ተመስገን ÷ ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን እንድታገኝ ኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁለቱ ሀገራት የመረጃና ፀጥታ ተቋማት የአጋርነት ስራዎችም ተጠናክሮ መቀጠሉ ቀጣናዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አቶ ተመስገን በስነ ስርዓቱ ላይ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የቀጠናውን ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ለማስጠበቅ በተቀናጀ ሁኔታ የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ተመስገን አያይዘው ገልጸዋል።

የብሄራዊ የመረጃና ደኀንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው ÷ ለደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፊሰሮች የተሰጠው ስልጠና የደቡብ ሱዳንን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘብ መንገድ የተሰጠ ሲሆን፤ በንድፈ ሃሳብና በተግባርም የተደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ተመሳሳይ ሥልጠና እንዲሰጥ ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራት ጥያቄ እየቀረበለት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወንድወሰን ÷ የአሁኑ ስልጠናም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በቀጣናው የመረጃና ደህንነት የልህቀት ማዕከል ለመሆን የያዘውን ራዕይ ለማሳካት እየሰራ መሆኑን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።

የደቡብ ሱዳን ናሽናል ሴኩሪቲ ሰርቪስ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ልዊስ ናታሊ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን መንግሥት ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ገልፀዋል፡፡

ወንድም የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የረጅም ዓመታት ድጋፍ ባይታከል ደቡብ ሱዳን አሁን ለምትገኝበት ደረጃ የማትደርስ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የደኀንነትና መረጃ ተቋማቶች የሚያደርጉት የመረጃ ልውውጥ እየተጠናከረ መምጣቱን የገለጹት ጀነራል ናታሊ÷ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፈሰሮች እየሰጠች ያለው ሥልጠናም እየተፈጠረ ያለውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክርና በቀጠናውም የሚኖረውን የደህንነት ስጋት ለመቅረፍ እገዛ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የደኀንነትና የመረጃ ተቋማት ትብብር እየተጠናከር በመምጣቱ ምክንያት በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ሽብርተኝነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ህገ ወጥ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ የተቀናጁ ሥራዎችን እየተሰሩ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ÷ በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነትና ትስስር ይበልጥ ለማስቀጠል በተለያዩ መንገዶች ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን የነጻነት ትግል ውጤት እንዲያስገኝ ዘርፈብዙ ድጋፎችን ስታደርግ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከነጻነት ወዲህም ባሉት ሂደቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተ ሲሆን ÷ በጋራ የፀጥታ ጉዳዮች፣ በባህል፣በኢኮኖሚና በሌሎችም ዘርፎች ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ የተለያዩ ስምምነቶች እንደተካሄዱ መግለፃቸውን የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.